የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ቦርድ ካለፈው የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን የሁለት ምክትል ዋና ጸሐፊዎች ሹመት ማድረጉን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት አቶ ካሣሁን ማሞ የንግድ ልማት እና የአድቮኬሲ ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሆነው ሲሾሙ አቶ ጀማል ሰይድ ደግሞ የአባላት እና ተቋማዊ ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሆነው ተሰይመዋል።
አቶ ካሳሁን በምክር ቤቱ ውስጥ ለ11 ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን፣ ማለትም የአድቮኬሲና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር እንዲሁም የውጭ ግንኙነትና ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ውስጥ አንጋፋ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ኤዲተር የነበሩ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ6 ዓመታት በከተማና ልማት ኢኮኖሚክስ መምህርነት ማገልገላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ጀማል ሰይድ በተለያዩ የግል ተቋማት ውስጥ በዋና ስራ አስፈጻሚነትና በምክትልነት የአመራር ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በዲንነትና በመምህርነት አገልግለዋል።
በ1939 ዓ.ም የተመሠረተው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀዳሚና አንጋፋ የንግድ ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል።
ተቋሙ የዓለም ንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን አባል በመሆን የዓለም አቀፍ ትስስር ያለው ሲሆን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ እንዲያድግና እንዲሰፋ የድጋፍና የጥቅም ተሟጋችነት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ይነገራል።
ቦርዱ በቅርቡ አቶ ዘካርያስ አሰፋን ዋና ጸሐፊ አድርጎ መሾሙ የሚታወስ ሲሆን፣ የአሁኑ የምክትል ዋና ጸሐፊዎች ሹመት የምክር ቤቱን የአመራር አቅም ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተገልጿል።
