እንግሊዝና ፈረንሳይ ጨምሮ 23 ሀገራት በጋዛ ያለው ጦርነት ‘አሁን ማብቃት አለበት’ ሲሉ አሳሰቡ።
ብሪታንያ፣ ፈረንሣይ ፣ጃፓን እና በርካታ የአውሮፓ ሀገራት በእስራኤል ላይ የበለጠ ጫና የሚፈጥር የጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን ቴልአቪቭ በጋዛ እያካሄደች ያለውን ጦርነት በአፋጣኝ ማቆም አለባት እንዲሁም እስራኤል የአለም አቀፍ ህግን ማክበር አለባት ሲሉ ሀገራቱ ተናግረዋል ።
በጋዛ ሰርጥ ከእርዳታ ማዕከላት ምግብ ለመቀበል ተሰልፈው የነበሩ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር መገደላቸው”አሰቃቂ” በማለት ሀገራቱ በጋራ አውግዘዋል።
በጋዛ የሚገኙ ሲቪሎች ሁኔታ አሳሰቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ጦርነቱ እንዲያበቃና ታጋቾች እንዲፈቱም ጥሪ ቀርቧል።
በጋዛ ያለው የእርዳታ አቅርቦት ስርዓት “አደገኛ” ከመሆኑም በላይ “የጋዛን ህዝብ ሰብአዊ ክብር እየተነፈገ” እንደሆነ በመግለጫቸው ሀገራቱ አሳስበዋል።
“የእርዳታ አቅርቦት መገደብ እና ሲቪሎችን ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ መግደል እናወግዛለን” ሲሉ ሀገራቱ በጋራ መግለጫቸው አስታውቀዋል።
እስራኤል በበኩሏ መግለጫው “ከእውነታው የራቀ” በማለት ውድቅ አድርጋዋለች።
ይሁን እንጂ፣ ከምዕራባውያን ሀገራት የመጣው ይህ ጠንካራ ውግዘት፣ በግጭቱ ዙሪያ የፖለቲካ ጫና የሚያሳይ ነው ተብሏል።
