በቅርቡ በቻይናው ቲያንጂን ኖርማል ዩኒቨርሲቲ ኪያንግ ዋንግ በተባሉ ፕሮፌሰር የሚመራ ቡድን አድርጎት በነበረው ጥናት አጫጭር ቪዲዮዎችን በብዛት መመልከት የትኩረት ጊዜን እስከ 47 ሰከንድ ብቻ ያደርገዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ ይህን attention fragmentation (የትኩረት መቋረጥ) ብለው ይጠሩታል፡፡
ተመራማሪዎቹ ዕድሜያቸው ከ17 – 30 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ አጫጭር ቪድዮን አብዝተው ይመለከታሉ ባሏቸው 112 ሰዎች ላይ የአእምሮ ስካን ካከናወኑ በኋላ የ“cognitive deficits” (የአእምሮ ማሰብ ፣ አገናዝቦ ውሳኔ የመወሰን ችሎታ ፣ የመረዳት፣ የመማር ችግር) እንዲሁም የድብርትና የጭንቀት ምልክቶችን አግኝተናል ብለዋል።
ከዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው በማታ አጫጭር ቪድዮ ለማየት የሚደረግ ስክሮሊንግ የእንቅልፍ ሆርሞንን (melatonin) ያዘገያል ፤ ይህም በመሆኑ በሂፕፖካምፐስ (hippocampus – ይህ ከአእምሮ የማስታወስ፣ የመማር፣ የስሜት ክፍል ጋር የተገናኘ ነው) እዚህ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖን ያሳድራል።
ይህ የአእምሮ ክፍል ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ በዋነኝነት አዲስ መረጃን ለማስቀመጥ ፣ ዝርዝሮችን ለማስታወስ የሚረዳ እንዲሁም በአጭር ጊዜ ያለውን ማስታወሻ ወደ ረጅም ጊዜ ማስታወሻ በመቀየር ትልቅ ሚና የሚጫወት የአእምሮ ክፍል ነው።
ተመራማሪዎቹ እነዚህ ለውጦች የአልኮል ሱስ በአእምሮ ላይ ከሚያስከትለው ጉዳቶች ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ይጠቁማሉ፡፡
አጫጭር ቪድዮዎችን ያለ ገደብ መመልከት በዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የሚያስከትለው ተፅእኖዎች ምንድን ናቸው ?
– ትኩረትን የመስጠት እና የማስተዋል ችሎታን ይቀንሳል፡፡
– ረጅም ፅሁፍ ማንበብ ፣ በእርጋታ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመከወን መሰላቸትን ያስከትላል፡፡
– ዝርዝሮችን በቀላሉ ለማስታወስ መቸገር ያመጣል።
– የእንቅልፍ እና የዕረፍት ጊዜን ያዛባል።
አጫጭር ቪድዮዎችን በብዛት መመልከት የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅእኖ እንዴት መቀነስ ይቻላል ?
° ዕለታዊ የስክሪን ጊዜ ገደብን መወሰን።
° ጤናማ እና ትምህርታዊ የሆኑ ይዘቶችን መምረጥ።
° እውነተኛ ደስታ የሚሰጡ እንደ ስፖርት መስራት፣ መፅሃፍ ማንበብ ፣ ከተፈጥሮ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ፣ ከወዳጆች ጋር መጨዋወት የመሳሰሉ ልምምዶችን ማዘውተር፡፡
ያስተውሉ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች በሙሉ ቋሚ ያልሆኑ ሲሆኑ ጤናማ የሆኑ የዲጂታል ልምምዶችን በመከተል የሚስተካከሉ መሆናቸውን ተመራማሪዎቹ ያስገንዘባሉ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ይህን መረጃ ያዘጋጀው ከሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ነው።
@tikvahethiopia
