የሕክምና ቁሳቁስ የያዘ የግብፅ አውሮፕላን ባሳለፍነው ዓርብ ነሐሴ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መደረሱን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ለኤርትራ የመድሃኒት አስተዳደር የተበረከተው ይህ እርዳታ፣ የዓይን ህክም እና የኩላሊት እጥበት መስሪያ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው። እርዳታው የቀረበው በግብፅ የልማት አጋርነት ኤጀንሲ አማካይነት መሆኑ ተመላክቷል።
እንደ ሚኒስቴሩ ገለፃ፤ ይህ ድጋፍ ካይሮ ከኤርትራ ጋር ያላትን “ስትራቴጂያዊና እህትማማች ወዳጅነትን” ለማጠናከር የምታደርጋቸው ጥረቶች አካል ነው።
የህክምና ቁሳቁስ እርዳታው ወደ አስመራ የተላከው፣ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጥቅምት ወር በአስመራ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ነው። ጉበኝቱ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ሁለቱም ሀገራት ገልፀዋል።
