የዩናይትድ ስቴትስ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ኢሌን ላርሰን አንዳንድ ሰዎች በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ የሚታጠቡ ቢሆንም፣ በየቀኑ የምንታጠብ ከሆነ የቆዳ መድረቅ እድላችንን ይጨምራል እንዲሁም ቆዳችን ለኢንፌክሽን የተጋለጠ እንዲሆን ያደርጋል ብላለች።
ባለሙያዎች የተሰነጠቀ ቆዳ ደግሞ ሁሉም ዓይነት ባክቴሪያ ወደ ሰውነታችን እንዲገቡ መንገድ እንደሚከፍት ግልጽ ነው ይላሉ።
ኢሌን በየቀኑ ገላን መታጠብ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ሰዎች ዘንድ የተለመደ የተሳሳተ ግንዛቤ እንደሆነ ታምናለች። ተደጋጋሚ ገላ መታጠብ ያለው ብቸኛ ጥቅም የላብ ጠረን ወይም የተለመደውን የሰውነት ጠረን ማስወገድ ነው።
ከጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የቆዳ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትን ዶ/ር ሲ. ብራንደን ሚቼልን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎችም ይስማማሉ። ገላ ስንታጠብ ቆዳችንን ከተፈጥሮ ዘይቶቹ እንደምናራቁት እና ይህም በሰውነታችን ውስጥ እና ላይ ባሉ ባክቴሪያዎች ላይ አለመመጣጠን እንደሚያመጣ ይናገራሉ።
አንዳንድ ባክቴሪያዎች ጠቃሚ ሲሆኑ፣ ሚዛናቸው ሲዛባ ጎጂ ሊሆን ይችላልም ብለዋል።
ሚቼል ለታይም እንደተናገሩት፡ “ሰውነታችን በጣም ፍጹም ነው፣ ልክ እንደ ጥሩ ዘይት እንደተቀባ ማሽን ነው። አብዛኛው ሰው ከልክ በላይ ገላውን ይታጠባል ብዬ አስባለሁ።” ይላሉ።
በየቀኑ ገላቸውን ለመታጠብ የሚመርጡ ሰዎች የግድ መተው ባይኖርባቸውም፣ በየጊዜው መላ ሰውነታቸውን በሳሙና ከመታጠብ እንዲቆጠቡ በጥብቅ ይመክራል።
እንደውም በብብት እና እግር ባሉ ጠረን ሊያመጡ በሚችሉ ቦታዎች ላይ ብቻ ሳሙና መጠቀም በቂ ነው። እንዲሁም በጣም የደረቀ ጸጉር ያላቸው ሰዎች በየጥቂት ሳምንታት አንዴ ብቻ መታጠብ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ነገር ግን የራስ ቆዳ ችግር ለምሳሌ ለፎሮፎር ላለባቸው ሰዎች በሳምንት ሁለት ጊዜ መታጠብ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
