የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይሰፍን ከመፈለግ እንዲሁም የባህር በር ጥያቄዎችን በማዳፍን ጫና ለመፍጠር እየሞከረ ይገኛል ፡፡
በኢትዮጵያ አስተማማኝ ዕድገት መምጣቱን ተከትሎ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ለማድረግም ይሞክራል፡፡ ይህንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት ለመንግስታቱ ድርጅት ደብዳቤ ለመጻፍ ተገዷል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይፋዊ ደብዳቤ ልኳል፡፡ ደብዳቤው ልክ እንደዚህ ቀደሙ የተለመደ ዓይነት የዲፕሎማሲ ጽኁፍ ካለመሆኑም ባሻገር በጥንቃቄ የተረቀቀ እና ከበዛ ትዕግስት ወደ ራስን መከላከል የተሻገረ አውድን የያዘ ሆኗል፡፡
ደብዳቤው ኢትዮጵያ ሰላምን ከመፈለግ እስከ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ድረስ የዘለቁ ሀሳቦችን ያካተተ ነው፡፡ ግራ ቀኙን የተመከተው ደብዳቤ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ቀለል አድርጋ በማየትም ሆነ በተለየ አካሄድ በፍጹም ሉዓላዊነቷን አሳልፋ መስጠት እንደማይገባትም ያትታል፡፡
ኢትዮጵያ ለጠባብ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል በቀጠናው መረጋጋት ላይ ቁማር ለሚጫወቱ ኃይላት በድብዳቤዋ ጠንካራ፣ ህጋዊ እና ሞራላዊ ግልጽ መስመሯን አስቀምጣለች፡፡ በጥቅሉ ደብዳቤው ማስጠንቀቂያንም፤ ማረጋገጫንም በማዕከልነት ይዟል፡፡
የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋገጋት እንዳይፈጠር ለማድረግ የተለያዩ ኃይላትን በመደገፍ ፀብ አጫሪ ድርጊት ውስጥ መሆኑን የሚትትው ደብዳቤው፣ ቀርተዋል የሚባሉ የህወሓት ሰዎች ጋር በመተባበር እንዲሁም የተለያዩ ታጣቂዎችን አይዟችሁ በማለት ላይ ይገኛል የሚል ይዘትንም አካቷል፡፡
ይህ ክስ በተደጋጋሚ የኤርትራ መንግስት ከሚያሳያቸው ባህሪያት አንጻር የመጣ እንጂ እንዲሁ ከመሬት ኢትዮጵያ ተነስታ ያደረገችው አለመሆኑንም ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ ሰኔ ላይ ለመንግስታቱ ድርጅት ከጻፈችው ደብዳቤ በኋላ ለአንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተላከው ጽሁፍ የኤርትራ መንግስት ችግሮችን እየደራረበ መምጣቱን እና ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን የሚጠቁም አድርጎታል፡፡
ተመሳሳይ የትንኮሳ ተግባራት በአስመራ በኩል እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ትላንትም፤ ዛሬም መኖሩን ገሀድ ያደረገም ነው፡፡ በሰዓቱ የነበረው ማስጠንቀቂያ ዛሬም ራሱን በደብዳቤ ደግሟል፡፡ ራስን በስርዓት መቆጣጠር እና መርህን መሰረት በማድረግ መገለጫው የሆነው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በጎረቤት አገር ቀጣይነት ባለው የውጥረት አካሄድም እየተፈተነ ይገኛል፡፡
በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥቅምት 2/2025 ለመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተጻፈው ደብዳቤ ይዘቱ ላይ ያተኮረም ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ትዝታዎችንም ያካተተ ነው፡፡
ለረዥም ጊዜ ውጥረት በማንገስ የሚታወቀውን የአስመራ መንግስት ሀሳብ እና የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ልምድን ታሳቢ ያደረገው ደብዳቤው ከ1998 እስከ 2000 የነበረውን የድንበር ለይ ጦርነትም አስታውሷል፡፡ የድንበር ለይ ጦርነቱን ተከትሎም ኢትዮጵያም እና ኤርትራ ሰለምም፤ ጦርነትም በሌለበት አውድ ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2018 ወደ ስልጣን ሲመጡ እንዲህ ዓይነቱን ውጥረት ለማብረድ ቁርጠኛ በመሆናቸው በአዲስ አበባ እና በአስመራ መካከል ፖለቲካዊ መረጋጋት መፈጠሩም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ እርቅ ለማምጣት ቁርጠኛ እንደነበረች እና በዛ ቅኝት ውስጥም መልካም ትስስርን መፍጠሯም ያስታወሳል፡፡ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዓለምን የሰላም ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ቀጠናው ወደ ሰላምና መረጋጋት ይሻገራል በሚል ተስፋ ተጥሎ ቢሰነብትም በኤርትራ መንግስት በኩል ያለው ቁርጥኝነት እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ፤ አሊያም ሙሉ ለሙሉ የኢሳያስ አፈወርቂ አስተዳደር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ችግሮች ባሉበት እንዲቀጥሉ አሉታዊ እድል ተፈጥሯል፡፡
ደብዳቤው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሚዛኑ እኩል አለመሆንንም በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
አሁንም ኤርትራ እንደትላንቱ የትንኮሳ መንገድን መከተሏን የሚያጋልጠው ደብዳቤው ሰላም እርባና ቢስ እንዳደረጋት ለተረዳችው አስመራ ዛሬም ቀጠናዊ አለመረጋጋትን መፍጠር ምርጫዋ እንዳደረገች ያትታል፡፡
ኤርትራ ከህዋሓት አክራሪ ኃይሎች ጋር በማበር እንዲሁም በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በማስታጠቅ በኢትዮጵያ ውስጥ እና በቀጠናው መረጋጋት እንዳይፈጠር እያደረገች መሆኑን አስገንዝቧል፡፡ ይህ ደግሞ ትንኮሳም ብቻ ሳይሆን በፕሪቶሪው ስምምነት የመጣውን ክልላዊ መረጋጋት እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተን አካሄድ ነው ይላል፡፡
በ2022 ህዳር ወር ላይ በፌደራል መንግስቱና በህወሓት ኃይሎች የተፈረመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ያስቆመ እና የፌደራል መንግስቱን የበላይነት ያረጋገጠም ነበር፡፡ ኤርትራ በዚህ ስምምነት ላይ ባለመካተቷ ደግሞ ውጥረቶች እንዲቀጥሉ በተለያየ ጊዜ ፍላጎቷን እያሳየች ይገኛል፡፡
አስመራ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አለመካተቷ ብሄራዊ አንድነትን ለማሳየት የተደረገ እንጂ እንዲሁ በአጋጣሚ እንዳልነበርም ተነግሯል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ኤርትራ ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም ጎን ለጎን የመኖር ውጥን አንደሌላት ጠቋሚ ያደርገዋል፡፡
ለመንግስታቱ ድርጅት ኢትዮጵያ የላከችው ደብዳቤ አዲስ አበባ ለሰላም ዛሬም ቁርጠኛ መሆኗን ያሰመረ ቢሆንም ትዕግስት መጨረሻ እንዳለውም የሚጠቁም ነው። ኢትዮጵያ እጅጉን በትዕግስት መቆየቷን የሚጠቁመው ደብዳቤው ይህ አካሄድ ግን እንደሚለወጥም ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ሰላም ፈላጊ፣ በምክንያት የምትንቀሳቀስ እንዲሁም ትዕግስትን በመላበስ ኃለፊነት የሚሰማት አገር ብትሆንም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እና ከተገደደች ቁርጠኛ እርምጃ እንደምትውስድም ለአንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተጻፈው ደብዳቤ ይጠቁማል፡፡ ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከልም የሚያረጋግጥላት ደብዳቤ ሆኗል ፡፡
ከኤርትራ መንግስት ትንኮሳ ባሻገር ደብዳቤው ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷን የተመለከተ ሀሳብም አካቷል፡፡ ኤርትራና አጋሮቿ እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ለትንኮሳ እንደቅድመ ሁኔታ አድርገው ቢወስዱትም ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚዋ እና ለነገዋ የባህር በሩን አጥብቃ እንደምትፈልገው በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
ደብዳቤው የአስመራን ትርክት መና ያስቀረም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ አብሮ ለመስራትና ለኢኮኖሚያዊ ትብብር እንጂ ኤርትራ እንደምትለው በፀብ አጫሪነት መረዳት ውስጥ አለመሆኑንም ያረጋገጠ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ራዕይ ሁሉን አካታች ብልጽግና ማምጣት እንጂ በራስ መንገድ የበላይ ለመሆን እንዳልሆነም ደብዳቤው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያ የምታምነው የአፍሪካ ቀንድ የወደፊት እጣ ፈንታዎች በትብብር ላይ መሰረቱን ያደረገ እንጂ በአለመተማመን ላይ ተመስርቶ መሆን እንደሌለባት አስምራበታለች፡፡
የኤርትራ መንግስት ባህሪ ከውጭ ኃይሎች ፍላጎት ጋር የማይላቀቅ በመሆኑ በተለይም ከግብጽ ጋር ያለው ግንኙነት ይህኑ መንፈስ ዳግም ያስተጋባ እና ያረጋገጠም ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በህዳሴው ግድብ ተስፋ የቆረጡት የካይሮ ፖለቲከኞች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠርን ዓላማቸው አድርገው ከያዙ ዋል አደር ብሏል፡፡ በተለይም ኤርትራ በቀይ ባህር መገኘቷ እና በአምባጋነን አገዛዟ ሳቢያ ለውጭ ተዋናዮች የተመቸች አጋር ያደርጋታል፡፡
በጥቅም እንጂ በርዕዮት ግንኙነት የሌለው ዲፕሎማሲን በመዘርጋትም ትታወቃለች አስመራ፡፡ ለዚህም ነው ኤርትራ የኢትዮጵያን እድገት፤ ግብጽ የኢትዮጵያን በራስ አቅም መልማትና ማደግ እየተቃወሙ ለመቀጠል የሚሹት፡፡ ምንም እንኳን ደብዳቤው የግብጽን ስም ባያነሳም፤ ካለው የጂዖፖለቲካ ውጥረት አንጻር በዚህ ልክ ማየቱ የተገባ መሆኑ ተወስቷል፡፡
ደብዳቤው ቁጣን ብቻ ሳይሆን ለችግሮችም መፍትሄ መምጣት እንዳለበት የሚያስገነዝብ ሀሳብንም አካቷል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት ስትቆም ትዕግስቷ መሟጠጡን ሊያሳይ በሚችል መንገድ ላይ ቆማ ብቻም ሳይሆን ዓለም አቀፍ ኃለፊነትንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሆነ ተነግሯል ፡፡
በዓለም ፖለቲካ ላይም ሆነ በመንግስታቱ ድርጅት ላይ ዓለም አቀፍ ኃላፊነትን እንዲሁም በትንኮሳ እና ራስን በመካላከል መካከል ያለውን ልዩነት በማሳየት የምትታወቅ መሆኗ ዛሬም ጉዳዮች በዛው ቅርጽ እንዲታዩ በር የሚከፍት ሀሳብ አቅርባለች፡፡
ከሁለትዮሹ ውጥረት ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ለሰላም ስለሚኖረው ተዓማኒነት እና የሰላም ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገው ደብዳቤው ኢትዮጵያ በትዕግስት ውስጥ ሆናም ቢሆን የጥንካሬ ቋንቋዋንም ያካተተ ሀሰብ ይዟል፡፡ ሉዓላዊነት ለድርድር እንደማይቀርብም ያሳያል።
በእርግጥ የኢትዮጵያን ትዕግስት እንደቸልተኛ አቋም ወስዶ የሚረዳ ካለ ታሪኳን እና ወኔዋን ያልተረዳ መሆን አለበት በሚልም ጽሁፉ ያስቀምጣል፡፡
ወረራን፣ የውስጥ አለመረጋጋትን እና ሌሎች ጫናዎችን መክታ እዚህ ላይ መድረሷን መረዳትም ያሸል ተብሏል፡፡ በራሷ መንገድ አሁንም ወደ ሰላም ጎዳና እየመጣች ያለች አገር ናትም ተብሎላታል ኢትዮጵያ፡፡
