የሚጠበቀው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ውጤትና መጪው ምርጫ

Date:

ሀገራችን ኢትዮጵያ በረዥም ጊዜ የሀገርነት ታሪኳ ምንም መንግሥት በሌለበት የሥርዐተ አልበኝነትና የመጠፋፋት ሒደት ውስጥ አልፋለች፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በየአካባቢው ባሉ ትናንሽ ባላባታዊ መንግሥታት ስር አልፈን ግዙፍና ጠንካራ ሀገረመንግሥት እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጦች ያሉበት ሥልጣኔም መሥርተናል። 

በዚህ የታሪክ ሒደት ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረትና ፍትሐዊነት እንዲነግሥ በርካቶች ታግለዋል። በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት የመንግሥት ሥልጣንን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለማረቅ ያለሙ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። 

ይኹን እንጂ ንጉሣዊውን ሥርዐት የተካው የደርግ መንግሥት ወደፊት የሚያይ፣ የተገራና ለሁሉም እኩል የሆነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዐት መፍጠር አልቻለም። በህወሓት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመናት ደግሞ ማኅበረሰብን በጠባብ የዘውግ መለኪያ ብቻ የሚያይ የአድሎ ሥርዐት ተፈጥሯል።

ይህም ዘውጋዊ የአድሎ ሥርዐት ሰላምና መረጋጋት ማምጣት ባለመቻሉ ውስጡ ባሉ ኃይሎች እና በሕዝባዊ አመጽ ለለውጥ የተዘጋጀ የሚመስል መንግሥትን ፈጥሮ ለሦስት ዓመታት በሽግግር መልክ ሀገሪቱን አስተዳድሯል፡፡

በእነዚህ ሦስት ዓመታት በለውጡ መንግሥት ሥር ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ ይኹን እንጂ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚፈታተኑ እንዲሁም የማዕከላዊ መንግሥቱን ቅቡልነት የሚያሳጡ ከፍተኛ ቀውሶችም ተከስተዋል፡፡ እንደ ሀገር በእነዚህ አስጨናቂ ክስተቶች አልፈን 6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫን አድርገናል፡፡

ፓርቲያችን ኢዜማ በወቅቱ የገለጻቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉ ኾነው፤ አንጻራዊ ቅቡልነት ያለው ማዕከላዊ መንግሥት መመሥረቱን ግን አልተቃወመም ነበር። ሀገር በጦርነት መካከል እያለፈች በነበረችበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት ማዕከላዊ መንግሥቱ የበለጠ እንዳይናጋ ሚናን መወጣት የኢዜማ ተመራጭ ስልት እንደነበር ይታወሳል፡፡

የመንግሥትን መመሥረት ተከትሎም ፓርቲያችን ከመንግሥት የቀረበለትን በጋራ እንሥራ ጥያቄ ሲቀበል፤ ከገዢው ፓርቲ ጋር ልዩነቶች እንዳሉት ከጠቀሳቸው ጉዳዮቸ መካከል “የሚሠራ ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር” ላይ የጋራ መግባባት ሊኖር እንደሚገባ በማስገንዘብ ነበር፡፡ 

ይህንን የልዩነት ሀሳብ ማጥበቢያ መንገድ የሆነውን እንዲሁም ሙሉ በሙሉ እንኳን ባይሆን ዋና ዋና በሚባሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ የሚያደርስ ሀገራዊ ምክክር መጀመሩን ፓርቲያችን እንደ ትልቅ እምርታ እና ተስፋ ሰጪ ሁነት ይመለከተዋል። በሒደቱ የታዩ ችግሮችን እየጠቆምን ልናደርግ የሚገባንን ተሳትፎም ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ከዚህም በኋላ በቀሩት መድረኮች ተሳትፏችንን እንቀጥላለን፡፡

በዚህ በትልቅ ተስፋ የተመለከትነው የሀገራዊ ምክክር ሒደት ማኅበረሰቡም በስፋት ተሳትፎበት፤ ከተለያየ አቅጣጫ እየተነሱ ያሉ ሀሳቦችና የቀረቡት አጀንዳዎች፤ የታረቀና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ከመፍጠር አንፃር ሊያመጣ የሚችለውን ውጤትም የበለጠ በጉጉት እንድንጠብቅ አድርጎናል።

እስካሁን ከተደረጉት ሰፊ ክልላዊ ውይይቶችም ሆኑ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች (የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ) ከቀረቡት አጀንዳዎች የምንረዳው ሀገራዊ ምክክሩ ሊመልሳቸው ከሚሞክራቸው ጉዳዮች ውስጥ የምርጫ አካሔድንና በጥቅሉ የፖለቲካ ስርዓቱን ሊቀይሩ የሚችሉ (ለምሳሌ ተመጣጣኝ ውክልና፤ ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት…ወዘተ) አጀንዳዎች ይገኙበታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በያዝነው ዓመት፤ በመጪው  ወራት፤ ሕገመንግሥታዊ ጊዜውን ጠብቆ የሚደረገው 7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫም እንዲሁ ከላይ ከተጠቀሰው የሀገራዊ ምክክር ሁነት ጋር ተደርቦ የሚመጣ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ሁኔታ ብዙ ወሳኝና ተያያዥ ጥያቄዎች ይዞ ይመጣል። እነኝህም፤

👉 መጪው ምርጫ የሚደረገው ከዚህ በፊት በነበረውና የምርጫዎቹን ተዓማኒነትና የህዝብ እውነተኛ ውክልና ጥያቄ ውስጥ የከተተው (ስለዚህም በሀገራዊ ምክክሩ ለመመለስ የሚሞከረው) ሥርዓት ነው? ወይንስ ሀገራዊ ምክክሩ በሥምምነት የሚቀይራቸውን ከፖለቲካና ከምርጫ ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ባካተተ ሁኔታ በአዲስ መልክ ነው የሚካሔደው?

👉 በአዲስ መልክ ነው የሚካሔደው ከተባለስ ሀገራዊ ምክክሩን በጊዜ ጨርሶና በዚያ ሥምምነት ውስጥ የተካተቱ ጉዳዮችን ሕጋዊ መሠረት ሰጥቶ (ለምሳሌ በሕዝበ ውሳኔ የሚወሰኑ ጉዳዮች ቢኖሩ) በአዲስ መልክ ምርጫ ለማካሔድ ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ ማጠናቀቅ ይቻላል ወይ?

👉 ያለው ጊዜ በቂ አይደለም ተብሎ ከታሰበስ፤ ይህን ብዙ ተስፋ የተጣለበትን የሀገራዊ ምክክር ውሳኔዎች ለቀጣይ ዐምስት ዓመት በዝምታ ሊታለፉ ነው ወይንስ ጊዜውን ለማሳጠር የሚወሰዱ ሕጋዊ መንገዶች አሉ?

የሚሉት ጥያቄዎች በጊዜ ውይይት ሊደረግባቸው የሚገባ እና መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው።

ይህንን ሀገር አቀፍ ምርጫ ልናሳካው ከምንፈልገው ዓላማ አንጻር በመመልከት እነዚህ የጊዜ ግብግብ ውስጥ የገቡ ተመጋጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች እንዴት ቢጓዙ የተሻለ ይሆናል? ይህንን በማድረግ ሒደት የሚነሡ ተግዳሮቶችስ በምን አይነት መንገድ ሊፈቱ ይችላሉ የሚለውን መንግሥት፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፣ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የሕግ ባለሙያዎች፣ የዐደባባይ ምሁራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደየሚናቸው መወያያ እንዲያደርጉት ፓርቲያችን ጥሪ ያቀርባል፡፡ ኢዜማ በዚህ ዙርያ በቅርቡ መሠል ውይይቶችን በማድረግ አቋሙንም እንደሚያሳውቅ ለመግለጽ ይወዳል።

በዚህ ወቅት ዋነኛ የፖለቲካ መወያያ ነጥብ መኾን የሚገባው ሀገራዊ ምክክሩ እና ሀገራዊ ምርጫው እንዴት ዓላማቸውን ሊያሳኩ በሚችሉበት ሁኔታ ሊከናወኑ ይገባል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ሀገራዊ ምርጫውንም ኾነ ሀገራዊ ምክክሩን በይድረስ ይድረስ አከናወኖ ዓላማቸውን እንዳይስቱ ማድረግ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ እንደኾነ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ( #ኢዜማ ) የተሠጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም.

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...