በአዲስ አበባ ዘንድሮ የሚጀመር አዲስ የኮሪደር ልማት የለም

Date:

በአዲስ አበባ ከተማ በዚህ ዓመት የሚጀመር አዲስ ኮሪደር ልማት እንደማይኖር የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። የከተማይቱ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት ከኮሪደር ልማት ጎን ለጎን ለመስራት ባለፈው ዓመት ከመረከቡ በፊት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በውጭ እርዳታ እና ዜጎች የተከናወነው ስራ “ሁለት ኪሎ ሜትር ብቻ” እንደነበር ከንቲባዋ ይፋ አድርገዋል። 

አዳነች ይህን ይፋ ያደረጉት ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 3፤ 2018 ዓ.ም በተካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው። የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት በዛሬው መደበኛ ጉባኤ ላይ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የኮሪደር ልማትን የተመለከተው ይገኝበታል።

ጥያቄውን ያነሱት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል፤ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን “ውብ እና ማራኪ አድርጓል” ሲሉ አድንቀዋል። የእዚህ ፕሮጀክት ተጽዕኖ ወደ ሌሎች ከተሞች መስፋፋቱን በበጎ ጎን ያነሱት የምክር ቤት አባሏ፤ ነገር ግን የኮሪደር ልማቱ “አሁንም ያልደረሰባቸው” የአዲስ አበባ አካባቢዎች እንዳሉ በመጥቀስ ጥያቄቸውን አስከትለዋል። 

“በእነዚህ የኮሪደር ልማት ያልደረሰባቸው አካባቢዎች፤ የኮሪደሩን ልማቱን ለማድረስ የከተማ መስተዳድሩ ምንድነው ያቀደው?” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ከንቲባዋ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። የኮሪደር ልማቱን የማስፋት ጥያቄ ወደ እርሳቸው ቢሮ ጭምር እንደሚመጣ በመጥቀስ ምላሻቸውን የጀመሩት ከንቲባ አዳነች፤ በተለይ ይህ የሚነሳው ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መሆኑን ለከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማን “የማደስ፣ የማዘመን፣ የማጽዳት” እንዲሁም “መሰረተ ልማቶችን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ስራ” ለሁሉም አካባቢዎች እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። “የተጀመሩት ስራዎች እና የተገኙት ውጤቶች ከከተማችን ስፋት አንጻር ገና ነው። ገና ከዚህ በላይ መስራት ይገባናል” ያሉት አዳነች፤ ነገር ግን ተመሳሳይ ስራዎች ሲሰሩ “እቅድ” እና “ዝግጅት” እንደሚያፈልግ ተናግረዋል። 

“እንደምታውቁት ቤት ያስፈልጋል፣ ለመሰረተ ልማቶቹ የበጀት ዝግጅት ያስፈልጋል። በጀቶቻችን ላይ ቅደም ተከተል ማስያዝ ያስፈልገናል” ሲሉ ለከተማይቱ ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም. “ትልቁ ትኩረት” የቤት ግንባታ እና የውሃ አቅርቦት መሆኑን ያመለከቱት ከንቲባዋ፤ ለዚህም የሚሆን በጀት የከተማይቱ ምክር ቤት ባለፈው መደበኛ ጉባኤው ማጽደቁን አስታውሰዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ባደረገው መደበኛ ጉባኤው ያጸደቀው በጀት 350.13 ቢሊዮን ብር ነበር። ከዘንድሮው የአዲስ አበባ በጀት ውስጥ ለቤቶች ልማት ዘርፍ የተመደበው 24.66 ቢሊዮን ብር ነው። የጸደቀውን በጀት ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ከንቲባ አዳነች በዛሬው መደበኛ ጉባኤ ላይ ይፋ አድርገዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የዘንድሮ በጀት ከዘርፎቹ ሁሉ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የተመደበለት የመንገድ ልማት ዘርፍ ነው። ዘርፉ 31.49 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለታል። የከተማይቱ አስተዳደር ዘንድሮ በሚገነባቸው መንገዶች “የኮሪደር ልማት ስታንዳርድን” እንደሚተገብር ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

“በአዳዲስ መንገዶቻችን ላይ የሳይክል መንገድ በሚያስፈልግበት ቦታ የሳይክል መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ ማስፋት፣ የተሽከርካሪ መንገዶች ስፋታቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ እናደርጋለን” ያሉት ከንቲባዋ፤ እነዚህ መንገዶች “ለዛሬው ችግር ማስተፈንሻ” ብቻ ሳይሆን “ከዘላቂ ልማት አንጻር” ግብዓት የሚያመጡ ተደርገው የሚገነቡ ይሆናል ብለዋል። 

አዳነች ለዚህ በማሳየነት የጠቀሱት አሁን በግንባታ ላይ ያለውን ከኡራኤል በቦሌ ብራስ አድርጎ እስከ ቦሌ አየር ማረፊያ የቪ.አይ.ፒ መግቢያ ድረስ ጋር የሚደርሰውን መንገድ ነው። የከተማይቱ አስተዳደር የጀመራቸውን መንገዶች “በጣም በፍጥነት” ከጨረሰ በኋላ የ“አዳዲስ” መንገዶች ግንባታ እንደሚጀምር ከንቲባዋ በዛሬው ማብራሪያቸው ላይ ቢያነሱም፤ በመንገድ የኮሪደር ልማት ረገድ ግን አዲስ ፕሮጀክት እንደማይኖር ገልጸዋል። 

“በዚህ ዓመት ኮሪደር ብለን፣ ለኮሪደር እንደ አዲስ የምንጀምረው አይኖረንም። ጥናት እናደርጋለን። ቤቶች እንገነባለን፣ በጥናታችን መሰረት ከህዝብ ጋር ቅድሚያ የምንሰጣቸው ቦታዎች ያልናቸው ላይ ውይይቶች እናደርጋለን” ሲሉ ከንቲባ አዳነች ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ በየካቲት 2016 ዓ.ም የተጀመረው የመጀመሪያው የኮሪደር ልማት፤ 48 ኪሎ ሜትር ገደማ የተሽከርካሪ መንገድን የሸፈነ ነበር። በዚሁ ምዕራፍ 96 ኪሎ ሜትር ገደማ የእግረኛ መንገድ በመንገዶች ግራ እና ቀኝ መሰራቱን እንዲሁም መቶ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የብስክሌት መንገድ መገንባቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅቱ አስታውቋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በነሐሴ 2016 ዓ.ም መጨረሻ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር የተከናወነለት ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት፤ 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 2,817 ሄክታር መሬት የሚሸፍን እንደሆነ አስተዳደሩ ገልጿል። ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ያካለለው ስምንት የአዲስ አበባ አካባቢዎችን ነው። 

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ዘንድ ከተማይቱን “የማዘመን” እና “የማደስ” ፕሮጀክት እንደሆነ ተደጋግሞ ቢገልጽም፤ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ግን ከፍተኛ ትችቶች ሲዘነዘሩበት ቆይቷል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኮሪደር ልማቱ ነዋሪዎችን “በግዳጅ የሚያፈናቅል ነው” ሲሉ ተችቶ ነበር። ለተፈናቀሉ ሰዎች ውጤታማ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስም ፕሮጀክቱ በአፋጣኝ እንዲቆም ባለፈው ሚያዝያ ወር ጥያቄ አቅርቦ ነበር። 

አምነስቲ በአዲስ አበባ ከተማ ሁለት ክፍለ ከተሞች ባደረገው ምርመራ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናት ከነዋሪዎች ጋር “በቂ ምክክር” አለማድረጋቸውን እና “ተገቢ ማስጠንቀቂያ” አለመስጠታቸውን እንደደረሰበት አስታውቋል። ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው በግዳጅ ከመፈናቀላቸው በተጨማሪ “ምንም አይነት ካሳ” አለማግኘታቸውንም በምርመራ ውጤቱ ላይ አመልክቷል። 

(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...

የአህጉሪቱን የርስ በርስ ንግድ ልውውጥ 250 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቀደ

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ፀሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ...

በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም

አሜሪካ እና ኢራን በተስማሙበት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ...

እስራኤል ጦሯ በደቡብ ሊባኖስ እንደሚቆይ አስታወቀች

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እንደተናገሩት፤ በአሜሪካ እና በኢራን...