በአውሮፓውያኑ 2025 ዓመት የኢትዮጵያ ከዓለማችን እጅግ ደካማ ገንዘቦች መካከል አንዱ ሆኖ የተመዘገበውና በዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ፓውንድ አቻው ጋር “ከአፍሪካ ደካማዉ የመገበያያ ገንዘብ” በሚል ከሁለት ቀናት በፊት በዓለም ባንክ በወጣ ሪፖርት ተጠቅሶ የነበረው የኢትዮጵያ ብር በቀጣዮቹ ወራት የመግዛት አቅሙ ሊሻሻል እንደሚችል ተገለጸ።
የወርቅ የዉጪ ንግድ ቀጣይነት በለው መንገድ እየጨመረ መምጣቱና በሀገሪቱ እየተካሄደ የሚገኜው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለብር የዋጋ መሻሻልና ጥንካሬ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውም ተመላክቷል።
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ መጀመሪያ መንግሥት የብር የምንዛሬ ተመን በገብያ እንዲመራ ከወሰነና የምንዛሬ መጠኑን ከጨመረ በኋላ የብር ዋጋ በሁለት ሦስተኛ የቀነሰ መሆኑን ያመላከተው የብሉምበርግ ዘገባ፤ ይሁን እንጂ የመንግሥት ባለስልጣናት ቅናሹ ጊዜዊ መሆኑን ነው የሚያምኑት ብሏል።
የብር መዳከም የተከሰተዉ ከዉጪ ምንዛሬ እጥረት እና ከዋጋ ግሽበት ጫናዎች ጋር ታይዞ ሲሆን ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የመጣው በተለይም የወርቅ ዉጪ ንግድ ገቢ መሻሻል በውጭ በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት በመሸፈን ለብሩ ዋጋ መሻሻል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የብሉምበርግ ዘገባ ገልጿል።
በመሆኑም ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ የመጣው የወርቅ የወጭ ንግድ ከቀደመው ዓመት ከነበረበት 409 ሚሊዮን ዶላር ባለፈው የሐምሌ ወር 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በመድረስ፤ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅ ከቡና የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኜቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) መናገራቸውን ጠቅሶ ጽፏል።
ይህም ሥራ አቁሞ የነበረው የሚድሮክ የወርቅ ማዉጫ ድርጅት ተመልሶ ሥራ እንዲጀምርና ትናንሽ የወርቅ አዉጪዎችም እንዲበረታቱ በማድረግ በህገ ወጥ የሚደረገዉን የወርቅ ማዉጣት ሥራ እንዲቀንስ በህጋዊ መንገድ የሚመረተው የወርቅ ምርት እንዲጨምር አስችሏል።
በሌላ በኩል የቡና የዉጪ ንግድ ገቢ ከ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ወደ 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር አድጓል።
የዉጪ ንግድ ገቢው ለመጨመሩ በምክንያትነት የተቀመጠው ኢትዮጵያ እየተገበረችው የሚገኜውና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሚደገፈው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሆኑ ተገልጿል።
እነዚህ እርምጃዎች መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የወጪ ምንዛሬ ተመኖች ላይ ያለዉን ልዩነት ያጠበቡት ሲሆን በዚህም ኢንቨስትመንት እና ንግድን አዳክሞ የነበረውን ችግር ማቃለለል መቻሉን ዘገባው አመላክቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ “ሕዝቡ በቅርቡ አወንታዊ ለውጥ ይጠብቅ” ሲሉም አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከብሉምበርግ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ደግሞ፤ እዮብ (ዶ/ር)፤ “ከብር ዋጋ መቀነስ ጋር ተያይዞ የባንክ ሥራን በዶላር ለሚያካሂዱ አካላት ደግሞ ስትራቴጃችሁን እንደገና እንድታጤኑት እላለሁ” ብለዋል።
ይህም በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በሀገር ውስጥ ገንዘብ፣ ብር እንዲተማመኑ ፍንጭ የሚሰጥ መልእክት መሆኑን ብሉምበርግ በዘገባው ጠቁሟል።
(አዲስ_ማለዳ)
