በዲጂታል የክፍያ ስርዓት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ የሚገኘው አሪፍ ፔይ 10 ሺሕ የክፍያ መፈፀሚያ መሳሪያዎችን ወይም “ፖስ ማሽኖችን” ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችለውን ስልታዊ የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
አሪፍ ፔይ ስምምነቱን የተፈራረመው ዓለም አቀፍ ክፍያና የገንዘብ ዝውውር ላይ ከሚሰራው ቪዛ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ መሰረተ ልማት እውን ማድረግ ላይ ከሚሰራው ኤቪኮም ጋር ነው፡፡
አሪፍ ፔይ ከአራት ዓመት በፊት እንደተመሰረተና ከሦስት ዓመት በፊት ደግሞ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሠጪ ተቋም ሆኖ በብሄራዊ ባንክ መመዝገቡን የገለጹት ዋና አስፈፃሚው ረድኤት ፅጌ፤ 10 ሺሕ የክፍያ መፈፀሚያ መሳሪያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት 3ቱ ተቋማት በትብብር ይሰራሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው የክፍያ መሳሪያዎቹን ግዥ ለመፈፀምና ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችለውን ገንዘብ ቪዛ እንደሚሸፍን የተናገሩ ሲሆን፤ ኤቪኮም ደግሞ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ ገጣጥሞ ያቀርባል ብለዋል፡፡
እስካሁን በመላ ሀገሪቱ ያሉት የክፍያ መፈፀሚያ መሳሪያዎች 18 ሺሕ ብቻ መሆናቸውን የገለጹት የአሪፍ ፔይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ እነዚህ ዘመናዊ የክፍያ መፈጸሚያ መሳሪያዎች ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥሩና አካታች የፋይናንስ ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያግዙ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሪፍ ፔይ ለመሳሪያዎቹ የሚሆነውን የሶፍትዌር ማበልፀግ ሥራ እንደሚሰራ የጠቆሙም ሲሆን፤ ይህም የንግድ ተቋማት፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሁሉንም አይነት የክፍያ አማራጮች በመጠቀም ክፍያዎችን በአንድ የክፍያ መፈፀሚያ መሳሪያ እንዲያከናውኑ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዋና ሥራ አስፈፃሚው እስካሁን ከ350 በላይ የክፍያ መፈፀሚያ መሳሪያዎችን በ18 ከተሞች በማሰራጨት ሲሰራ ቆይቷል ያሉ ሲሆን፤ በቀጣይም በ10 ሌሎች ከተሞች ላይም ተደራሽ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሪፍ ፔይ ከዲጂታል ክፍያ ስርዓት በተጨማሪም የንግድ ተቋማት ሕጋዊ የንግድ ፈቃዳቸውን በመጠቀም ምርቶቻቸውን ለደንበኞቻቸውን የሚያቀርቡበትን “አሪፍ ሾፕ” የተሰኘ የኦንላይን ግብይት አማራጭ በቅርቡ ይፋ ማድጉም ተገልጿል፡፡
አሐዱ ራዲዮ
