ኖርዌይ የኤርትራን መንግሥት የሚደግፉ ትውልደ ኤርትራውያንን ዜግነት እንደምትነጥቅ አስታወቀች

Date:


የኖርዌይ የስደተኞች አገልግሎት ተቋም እንዳስታወቀው፤ ለሁለት ዓመታት ምርመራ ካደረገ በኋላ የኤርትራን መንግሥት የሚደግፉ ኖርዌጅያን-ኤርትራውያንን ዜግነት ለመንጠቅ ወስኗል።

የኖርዌይ ዜግነት የተሰጣቸው ኤርትራውያኑ ለኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ይሰጣሉ ያለው አምስት አባላት ያሉት መርማሪ ኮሚቴ ነው። 135 ኤርትራውያን ላይ ምርመራ ያደረገ ሲሆን፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጽፉትን እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ስለ እነሱ የሚናገሩትን ተከታትሏል።

ምርመራ የተደረገባቸው 135 ሰዎች የኖርዌይ ዜግነት የተሰጣቸው ሲሆኑ፤ ላለፉት ስምንት ዓመታትም በአገሪቱ ኖረዋል። እስካሁን ድረስ 20 ሰዎች መኖሪያ ፈቃዳቸውን ሲነጠቁ፤ የሌሎች 30 ሰዎች ጉዳይ ደግሞ እየተመረመረ ነው።

በአጠቃላይ ምን ያህል ሰዎች ዜግነታቸውን እንደሚነጠቁ ግልጽ አይደለም።

በኖርዌይ ሕግ መሠረት፤ በአገሪቱ ጥገኝነት የጠየቁ ሰዎች የሚሰጣቸው የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ዜግነት ሊነጠቅ ይችላል። የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ዜግነት የተሰጣቸው ስደተኞች አንዳች ስህተት ከተገኘባቸው ውሳኔው ሊቀለበስ እንደሚችል ሕጉ ይደረጋል።

የኖርዌይ መንግሥት የትውልደ ኤርትራውያንን የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ዜግነት ሲነጥቅ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ኤርትራውያን በትውልድ አገራቸው ሳሉ ለግዳጅ ውትድርና፣ ለእስራት፣ ለብዝበዛ እና ለስቅይት እንደሚጋለጡ በመጥቀስ በኖርዌይ ጥገኝነት ከጠየቁ በኋላ ለኤርትራ መንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጡ ተገልጿል።

የኖርዌይ የስደተኞች አገልግሎት ተቋም እንዳለው፤ ኤርትራውያኑ ለኖርዌይ መንግሥት የገለጿቸው የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና እስራት ትክክለኛ አይደሉም።

የኖርዌይ መንግሥት ምርመራ የከፈተው በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል ከሁለት ዓመታት በፊት በተነሳው ግጭት ምክንያት ነው። በዚህ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩ ኤርትራውያን አንዱ እአአ በ2013 በኖርዌይ ጥገኝነት ያገኘ ግለሰብ ነው።

የኖርዌይ የስደተኞች አገልግሎት ተቋም እንዳለው፤ ትውልደ ኤርትራውያኑ ላይ የተካሄደው ምርመራ በዋነኛነት ያተኮረው ለመንግሥት ድጋፍ በሚሰጡት ላይ ነው። በኦስሎ እና በርገን ከተሞች በመዘዋወር ምርመራውን ያካሄደ ሲሆን፤ በርገን ከዚህ ቀደም በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል ግጭት የተከሰተባት ከተማ ናት።

የኤርትራን መንግሥት የሚደግፉ ስደተኞች ላይ ምርመራ ከተከፈተ በኋላ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ በድጋሚ ምርመራው መጀመሩ ተገልጿል። ከአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት በኋላ የኤርትራውያኑ ይግባኝ እንደሚታይ የኖርዌይ የስደተኞች አገልግሎት ተቋም አስታውቋል።

በምርመራው ወቅት ስደተኞቹ ለምን የጥገኝት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አገኘ? ለምን የሸሹትን መንግሥት ይደግፋሉ? የሚሉትም መፈተሻቸው ተገልጿል። መርማሪ ቡድኑ ከማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፎች በተጨማሪ ኖርዌይ ከሚኖሩ እና የኤርትራን መንግሥት ከሚቃወሙ ትውልደ ኤርትራውያን ጥቆማ ሰብስቧል።

ለጥገኝነት ጥያቄ የተሳሳተ መረጃ ያቀረቡ ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ እና ዜግነትም ሊሰረዝ ይችላል። ወደ እስራኤል በሕገ ወጥ መልኩ የገባ እና የኤርትራ መንግሥትን በመደገፍ ይታወቃል የተባለ ኤርትራዊ ባለፈው ወር ወደ አገሩ መባረሩን የእስራአል መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው ይታወሳል።

እስራኤል የኤርትራ ዜግነት ያለው እና የመንግሥት ደጋፊ የሆነን ግለሰብ ከአገሯ ስታባርር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የአንድ ልጅ አባት የሆነው ኤርትራዊ ወደ እስራኤል የገባው በአውሮፓውያኑ 2011 ሲሆን፤ ላለፉት 14 ዓመታት ኑሮውን በዚያው አድርጎ ቆይቷል።

እ.አ..አ በ2023 በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ በኤርትራውያን መካከል በተከሰተ ግጭት እስራኤላዊ ፖሊስን ጨምሮ 150 ሰዎች መጎዳታቸው ይታወሳል።

የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች ጎራ ለይተው በተሳተፉበት ግጭት 11 ሰዎች በጥይት ተመትዋል። እ.አ.አ በ2024 በነተሳ ግጭት ደግሞ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ስምንት ሰዎች ክፉኛ መቁሰላቸው አይዘነጋም። NBCEthiopia

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...