ውሳኔው ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶችንም ያካትታል ተብሏል
ዘንድሮ በአዲስ አበባ በሚሰጡ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተናዎች አፋን ኦሮሞ እንደሚካተት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በአዲስ አበባ ለሚገኙ አሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች የትምህርት ጽሕፈት ቤቶች ማሳወቁን ሪፖርተር የተመለከተው ደብዳቤ ያሳያል። ደብዳቤው በመንግሥት፣ በግልና በዓለም አቀፍ (International) አስፈታኝ ትምህርት ቤቶቹም ዝግጅት እንዲያደርጉ ያሳስቧል፡፡
ለ8ኛ ክፍል አማርኛና አፋን ኦሮሞ እንደ አንደኛ ቋንቋ እንደሚሰጡ በደብዳቤው ሲመላከት የሒሳብ ፣ የእንግሊዝ ፣ የሳይንስና የዜግነት (ግብረገብ) ትምህርቶችም ይሰጣሉ ይላል ።
የ6ኛ ክፍል ፈተና በአማርኛ ሥርዓተ ትምህርት ለሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች አማርኛ እንደ አንደኛ ቋንቋ ሲሰጥ፤ አፋን ኦሮሞ ደግሞ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ይሰጣል፡፡
የ6ኛ ክፍል ፈተናን በአፋን ኦሮሞ ሥርዓተ ትምህርት ለሚያስተምሩት ደግሞ አፋን ኦሮሞ እንደ አንደኛ ቋንቋ ሲሰጥ፣ አማርኛ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ይስጣል፡፡ ሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ሒሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ አካባቢ ሳይንስና ግብረገብ ተመሳሳይ ናቸው፡፡
ደብዳቤውን የፈረሙት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዲናኢል ጫላ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ተጠይቀው፣ «ጉዳዩ የሚመለከተው ሌላ ስው ነው፤›› ብለዋል፡፡ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት አቶ አበበ ደግሞ፣ ‹‹ስለጉዳዩ ማጣራት ይኖርብኛል›› በማለት ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሪፓርተር ጋዜጣ
