“ይኼ ኮሌጅ ለእኛ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካም ጭምር የሚጠቅም ነዉ”

Date:

ልጅ ኤልያስ ጥላሁን
(የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ መሥራች)

የዛሬው እንግዳችን ልጅ ኤልያስ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ›› ለመክፈት እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ሰው ናቸው፡፡ ለመኾኑ እንዲህ ያለው መሻታቸው ከየት ተወለደ? ትልሞቻቸውና ግቦቻቸውን ወደ ተግባር ለመተርጎምስ ምን ዐይነት ምዕራፎችን አለፉ? የእንቅስቃሴያቸው አሁናዊ ቁመናስ ምን ይመሥላል? በሚሉት ጥያቄዎች ዙርያ የሚከተለውን ሰፋ ያለ ቆይታ ከግዮን ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኀተመወርቅ ጋር አድርገዋል፡፡ እንኾ! (ክፍል ሁለት )

ግዮን፡- ለምንድነው የዩኒቨርሲቲያችሁ መጠሪያ ስም ‹‹ልጅ ኤልያስ›› የኾነው?


ልጅ ኤልያስ፡- ብዙ ሰዎች በራሳቸው ስም ተቋሞቻቸውን ይሰይማሉ፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ ‹‹ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ›› ነበር የሚባለው፡፡ በምኒልክ ስምም በርካታ ተቋማት ተሰይመው ይገኛሉ፡፡

ከነገሥታቱ ውጪም በርካታ ግለሰቦች የመሠረቷቸውን ተቋሞች ስያሜያቸውን በራሳቸው ስም ያደርጋሉ፡፡ አንድ ተቋም ባለቤት ይፈልጋል፡፡ የተቋሙ ባለቤት ደግሞ ተቋሙን በደንብ ይንከባከባል፡፡ እኔ አጀማመሬ የሳይንስ ትምህርቶችን በሙሉ ወደ አማርኛ ቀይሮ ማስተማር ነው፡፡ ይህንን ከዚህ ቀደም ማንም ሰው አላደረገው፡፡ በዚህም ምክንያት በራሴ ስም ልሰይመው በቅቻለሁ፡፡


አሁን ላይ አሜሪካ ያለሁ በመኾኑ አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ ለሟሟላት ዕድሉ አለኝ፡፡ እንደሚታወቀው በአሜሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ፡፡ አሁን ያለሁበት የኮሎራዶ ግዛት ውስጥም በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ እዚያ አካባቢ ላይ የሚያስፈልገንን የፋይናንስ ድጋፍ የምናገኘው ከዚሁ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ አሜሪካን ሀገር ከኮሚኒቲውም በላይ ትልልቅ ተቋማትም ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

ብዙ የፊልም አክተሮች፣ ኳስ ተጫዋቾች አፍሪካን ለመርዳት ብለው እንዲህ ዓይነት ነገር ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ይኼ ኮሌጅ ለእኛ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካም ጭምር የሚጠቅም ነው፡፡ በራሳችን ቋንቋ ተምረን በራሳችን መንገድ መጠቀም ይኖርብናል፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ ዕውቀት ያላቸው የኢትዮጵያ ልጆችን አንጠቀምባቸውም፡፡ ዕውቀታቸው ለባዕዳን በባዕዳን ሀገር ባክኖ ይቀራል፡፡ ሀገር ብዙ ዋጋ ከፍላ አስተምራቸው፣ ተገቢውን ወረታ ሳታገኝ የሌሎች ሀገራት ሲሳይ ኾነው ይቀራሉ፡፡


ግዮን፡- የተቋችሁ አመሠራረት እንዴት ነበር?

ልጅ ኤልያስ፡- ከተመሠረተ ሁለት ወር ኾኖታል፡፡ የተመሠረተው ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ነው፡፡ ገና አዲስ ተቋም ነው፡፡ የመጀመሪያ ሥራችን የሳይንስ ቃላትን ማግኘትና መሥራት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ የተሠሩ ጥናቶችን አግኝተናል፡፡

ወደ 15 ሺህ 87 የሚኾኑ የሳይንስ ቃላት አግኝተንበታል፡፡ በግብርና፣ ኬሚስትሪ፣ ጂኦሎጂ፣ ጆኦግራፊና ሌሎች ወደ 13 ሙያዎች የተካተቱበት ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት እርዳታና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ በ1989 የተዘጋጀ መዝገበ ቃላትም አግኝተናል፡፡ አሁን በዚህ መልክ በማሰባሰብ ላይ ስንኾን፣ በቀጣይ ደግሞ ካሪኩለም እናዘጋጃለን፡፡ ዓላማችን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ይህን ኮሌጅ ኢትዮጵያ ውስጥ መመሥረት ነው፡፡


ሥራውን መጀመር የፈለግነው በደንብ አደራጅተን ነው፡፡ ተቋሙን ለመመሥረት ሳስብ ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎችን ፈልጌ ነው የመጣሁት፡፡ በአፍሪካና በኢትዮጵያ ደረጃ አስፈላጊ የኾኑ የዝግጅቱ ሥራ ስንሠራ የሚያስፈልጉ ሰዎች ናቸው የመረጥናቸው፡፡ ከሰሞኑ በጣም ጥሩ ዜና ሰምተናል፡፡ ይኸውም በአዲስ አበባ ከተማ ከ4 ኪሎ እስከ ሽሮ ሜዳ ‹‹የዩኒቨርሲቲ መንደር›› ተብሎ መሰየሙ ነው፡፡

ይህ ለኛ ትልቅ ነገር ነው ፤ በዚያ አካባቢ ቦታ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቦታ ማግኘት ትልቅ ችግር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ደግሞ የአማርኛ ኮሌጅ ሲባል ግር ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱም አማርኛን አንድ ክልል አካባቢ ነው የሚጠብቁት፡፡ ነገር ግን አማርኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ ሰፊ ተናጋሪ ያለው ቋንቋ ነው፡፡


መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁን ላይ ዐማርኛን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይናገረዋል፡፡ ይህ መኾኑ ብዙዎች በሚያውቁት ቋንቋ ጠጣር የሚመስሉ የሳይንስ ጽንሠ ሐሳቦችን እንዲረዱ ያግዛቸዋል፡፡ የእኛ ሀገር ሰው በአብዛኛው በእንግሊዘኛ ስለኾነ የሚማረው ለመረዳት እጅግ ይቸገራል፡፡ አሁን ግን በዚህ ችግር ዙሪያ እልባት ለመሥጠት፣ ችግሩን የሚረዱ ወገኖች እየሠሩበት ይገኛሉ፡፡

ከእኛ ጋር እየሰሩ ያሉትንም ሰዎች ካሪኩሉም እንዲያዘጋጁ መመሪያ እንሰጣቸዋለን፡፡ ይህ ከኾነ በኋላ ብዙ ነገሮችን አገር ውስጥ መሥራት ይቻላል፡፡ እነቻይና፣ እነጃፓንና መሰል የሩቅ ምሥራቅ ኤዢያ ሀገራት በአንድ ጊዜ ያደጉት ሳይንስን በራሳቸው ቋንቋ ማስተማር ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ ሳይንስን በባዕድ ሀገር ቋንቋ ሀገር ውስጥ ማስተማር ከባድ ነው፡፡


ግዮን፡- ከእናንተ ጋር የሚሠሩት ሰዎች እነማን ናቸው? እንዴትስ ተመረጡ?


ልጅ ኤልያስ፡- በመጀመሪያ እኔ ስለሥራው ሳስተዋውቅ በጣም በርካታ ሰዎች የትምህርት ማስረጃዎችን ልከውልኛል፡፡ ኢንጅነር አምቦሎ እንዳለው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እንዲሠራልን የተመደበ ነው፡፡ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ኢንጂነር ነው፡፡ በነገሩ ላይ ጥልቅ የኾነ መረዳት አለው፡፡ እኔ መጀመሪያ ቃለመጠይቅ ካደረግኩት በኋላ በሳምንት አንድ ቀን ውይይት እናደርግ ነበር፡፡

ሁለተኛዋ ሰው ሙሉዓለም ታምሬ የምትባል እህታችን ነች፡፡ የራሷ መንግሥታዊ ያልኾነ የእርዳታ ድርጅት አላት፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብዙ ዓመት ሠርታለች፡፡ የላከችልን ሲቪም ከሚገባው በላይ ብቁ መኾኗን የሚያሳይ ነው፡፡ እሷ በአፍሪካ ላይ የሾምናት ዳይሬክተር ነች፡፡

ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ውጪ በሌሎች የአፍሪካ ከተሞችም አሠራራችንን እናስተምራለን ፤ እናስተዋውቃለን፡፡ ዕቅዳችንም ብዙ ኢንዱስትሪዎች ሊቋቋሙ የሚችሉበት የሳይንስና ምህንድስና ትምህርት እናስተምራለን የሚል ነው፡፡ ይኼ ደግሞ፣ ወደፊት በአፍሪካ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ሊያመጣ የሚችል ነገር ነው፡፡

ግዮን፡- ቢሮ ከፍታችኋል?

ልጅ ኤልያስ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ለመክፈት ገና በጥናት ላይ ነን፡፡ የአፍሪካውም ቢሮ አዲስ አበባ ስለሚኾን እያጠናን ነው፡፡ በከተሞች ደረጃም የተለያዩ ከተሞችን በማቀናጀት እንሠራለን እንጂ በእያንዳንዱ የአፍሪካ ከተማ የመመሥረት እቅድ የለንም፡፡ የያዝነው ሥራ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን በአምስት ዓመት ውስጥ ሁሉንም ነገር ጨርሰን ወደተሳለጠ ሥራ ውስጥ እንገባለን የሚል ተስፋ አለን፡፡

ግዮን፡- በደብረ ብርሃንም ቢሮ የመክፈት እቅድ እንዳላችሁ ይነገራል፡፡ ምን ይላሉ?

ልጅ ኤልያስ፡- ዩኒቨርሲቲውን በመጀመሪያ መክፈት የፈለግነው ሦስት ቦታዎች ላይ ነው፡፡ በደብረ ብርሃን፣ ቡታጅራና አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ከሦስቱ በአንዱ ከተማ ቀድመን እንጀምራለን፡፡ አዲስ አበባ ቦታ ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከአዲስ አበባ ይልቅ ደብረ ብርሃን ላይ ለመክፈት አቅደን ነበር፡፡

ምክንያታችን ደግሞ፣ የመጀመሪያው ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ ብዙ ስለማይርቅ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ኃይሌ ሚናስ›› የተባለው አካዳሚ እዚያ በመኖሩና ተማሪዎቹም ከመላው ሀገሪቱ ተወዳዳረው ትልቅ ውጤት በማምጣት እዚያ የገቡ በመኾናቸው፣ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ ውጭ ሀገር ከሚሄዱ አጠገባቸው ኮሌጃችንን ከፍተን ተቀብለን የማስተማር ዕቅድ ስለሰነቅን ነበር፡፡

በዚያ ላይ ደብረ ብርሃን ቦታ የማግኘት እድላችን ሰፊ ነው ብለን አምነን ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን መንግሥት ያስተዋወቀው የዩኒቨርሲቲ መንደር፣ ለእኛ ትልቅ ተስፋ ፈጥሯል፡፡ በዛ ላይ ማዕከላችን አዲስ አበባ ቢኾን ለሁሉም አመቺ ነው፡፡ ከተለያዩ ከተሞች ተማሪዎች መጥተው ለመማርም ያስችላቸዋል፡፡


ግዮን፡- ዩኒቨርሲቲውን እንደተቋም ስትከፍቱ ከመንግሥትና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ተነጋግራችኋል?

ማስታወሻ፡- ውድ አንባቢያን ከልጅ ኤልያስ ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ ቀጣዩን ክፍል በሚቀጥለው ዕትም ይዘን የምንቀርብ ይኾናል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...

“እኔ እስካለሁ ድረስ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም!”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ሰኔ 5 ቀን...

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...