የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ካሚል ኢድሪስ፣ በሱዳን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ከሚያዚያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥታቸው መቀመጫ ወደ ሆነችው ካርቱም መመለሱን እሁድ ዕለት አስታወቁ።
መንግሥታቸው ላለፉት ሦስት ዓመታት የሀገሪቱን ጉዳዮች ሲያከናውን የቆየው በምሥራቃዊቷ የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳን ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን ካርቱም ባህሪ በተባለ ስፍራ ለተሰበሰበው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር “መንግሥት ወደ ሃገሪቱ ዋና ከተማ ተመልሷል” ብለዋል።
በተጨማሪም በጤና እና በትምህርት ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል፣ ሆስፒታሎችን እንደገና ለመገንባት፣ እንዲሁም የካርቱም ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጎርጎሮሳውያኑ 2026 “በሱዳን የሰላም ዓመት” እንደሚሆን ጠቁመው፣ ለዳግም ግንባታና ልማት የታቀዱ ዕቅዶችን፣ የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ እና የሱዳን ፓውንድ የምንዛሬ ተመን በማረጋጋት ኢኮኖሚውን ለማሻሻል የተያዙ ጥረቶችን ይፋ አድርገዋል።
የመንግሥታቸው መመለስ በዋና ከተማዋ አስተዳደራዊ ሥራዎችንና የመንግሥት አገልግሎቶችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።
ይህም በቅርብ ወራት ውስጥ የመንግሥት ተቋማትን ቀስ በቀስ ወደ ሥራ ለመመለስ ከወጡ ዕቅዶች እና በአንዳንድ አካባቢዎች ካለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ጋር የተያያዘ መሆኑ ተጠቁሟል።
ካርቱም በመንግሥት ተቋማት፣ በመሠረተ ልማት እና በመሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተሉ ብርቱ ውጊያዎችን አስተናግዳለች።
በሱዳን ጦር (SAF) እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል በካርቱም ውጊያ ከተቀሰቀሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ የሱዳን መንግሥት በጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 2023 መጨረሻ ላይ ወደ ፖርት ሱዳን ተዛውሮ ነበር።
ዝዉውሩ በሂደት የተከናወነ ሲሆን፣ የሉዓላዊ ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲሁም በርካታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ዋና ዋና መሥሪያ ቤቶች ወደ ፖርት ሱዳን ተዛውረዋል፣ በዚህም ፖርት ሱዳን በካርቱም በነበረው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በወቅቱ የአገሪቱ ጉዳዮች የሚመሩባት ማዕከል ሆና ቆይታለች።
በግንቦት ወር 2025 የሱዳን ጦር የካርቱም ከተማ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይል ነፃ መደረጉን ያወጀ ሲሆን፣ ይህም ከተማዋ ቀስ በቀስ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችን እንድታገኝና ነዋሪዎችም ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ መንገድ ከፍቷል።
ግጭቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ደግሞ በሱዳን ውስጥና ከሃገር ውጭ እንዲሰደዱ አድርጓል ሲል ዢኑዋ ዘግቧል።
