አብዛኞቻችን ውኃን እንደ ቀላልና በማንኛውም ጊዜ እንደማይጠፋ ሀብት አድርገን እንመለከተው ይሆናል። ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ አደገኛና የተሳሳተ መሆኑን አሁን ያለው የዓለም ተጨባጭ እውነታ ያረጋግጣል። አሁን ላይ ውኃ ከምንጠጣው መጠጥ በላይ የዓለም ሕልውና የተመሰረተበት ታላቅ ሀብት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ዓለም ውጤቱ ሊቀለበስ የማይችል የውኃ ዕዳ ውስጥ መግባቷን ገልጿል። ይህ ሁኔታ ከዚህ በፊት በምናውቃቸው “የውኃ እጥረት” ወይም “ቀውስ” በሚሉ ቃላት ሊገለጽ የማይችል ከባድ ደረጃ ላይ ደርሷል። ዓለም ወደ “የውኃ ዕዳ” (Era of Water Bankruptcy) ዘመን ገብታለች ነው የተባለው።
“የውኃ ዕዳ” (Water Bankruptcy) ማለት ምን ማለት ነው?
ተፈጥሮ በዝናብ መልክ ከምትሰጠው “ገቢ” በላይ፣ ዓለማችን እራሳቸውን መተካት ከሚችሉበት ፍጥነት በበለጠ የወንዝ እና የከርሰ ምድር ውኃን በማውጣት በመጠቀሟ የመጣ ቀውስ ነው። ልክ ከገቢ በላይ ወጪ በማውጣት ዕዳ ውስጥ እንደሚገባ ድርጅት፣ ምድራችንም የውኃ ክምችቷን አሟጣ እየጨረሰች ነው።
በዚህ ቀውስ ሳቢያ በርካታ ከተሞች የህልውና አደጋ ተጋርጦባቸዋል። የአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል የከርሰ ምድር ውኃዋን አሟጣ በመጨረስ ረገድ የምድራችን የመጀመሪያዋ ዘመናዊ ከተማ ለመሆን ከጫፍ ደርሳለች።
ሜክሲኮ ሲቲ ደግሞ ከመሬት ውስጥ ውኃ በከፍተኛ ሁኔታ በመውጣቱ ምክንያት መሬቷ እየዛለ በየዓመቱ በ20 ኢንች እየሰጠመች ትገኛለች። በአሜሪካም ቢሆን ለሚሊዮኖች ሕይወት መሠረት የሆነው የኮሎራዶ ወንዝ መጠን በየጊዜው መቀነሱ ለሀገሪቱ ትልቅ ስጋት ሆኗል።
ከ1990ዎቹ ወዲህ 50 በመቶ የሚሆኑት የፕላኔታችን ትላልቅ ሐይቆች ውኃቸውን አጥተዋል፤ እንዲሁም 70 በመቶ የሚሆነው የከርሰ ምድር ውኃ ክምችት በተከታታይነት እየቀነሰ መጥቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ላለፉት 50 ዓመታት በአውሮፓ አህጉር ስፋት ልክ የነበሩ እርጥበታማ መሬቶች ከምድር ገጽ ጠፍተዋል። በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዙሪያ 4 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በዓመት ውስጥ ቢያንስ ለአንድ ወር ከፍተኛ የውኃ እጥረት ይገጥማቸዋል።
ሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ በችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቂ ቢሆኑም፣ መላው ዓለም ውኃን በነፃ እንደሚገኝ ተራ ነገር ከማየት መላቀቅ እንዳለበት ተገልጿል።
Source: UN, CNN
|@tikvahethmagazine
