በቬኔዙዌላው ድንበር አቅራቢያ በተከሰከሰው አዉሮፕላን ፖለቲከኞች እና የህግ አዉጪ ባለሙያዎችን ጨምሮ የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተዘግቧል።
ከሟቾቹ መካከል የ36 ዓመቱ የኮሎምቢያ የተወካዮች ምክር ቤት የካታቱምቦ ክልል ተወካይ የሆኑት ዲዮጀነስ ኩንቴሮ አማያ ይገኙበታል ተብሏል።
በመጋቢት ወር ሊካሄድ በታቀደው የኮንግረስ ምርጫ እጩ የነበሩት ካርሎስ ሳልሴዶ በአዉሮፕላኑ አደጋ ህይወታቸዉ ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአዉሮፕላን አደጋዉን ምክንያት ለመመርመር አደጋዉ የደረሰበት አካባቢያዊ መልክአምድር አስቸጋሪ መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት እየተናገሩ ሲሆን፤ ይህ የነፍስ አድን ስራዉን እንደገታዉ ገልፀዋል።
ባለሥልጣናቱ የአደጋውን መንስኤ እስካሁን ያልገለጹ ሲሆን፤ የአውሮፕላኑ የድንገተኛ አደጋ መብራት አደጋዉ ከመከሰቱ በፊት እየሰራ አልነበረም ተብሏል።
የኮሎምቢያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አውሮፕላኑ በቦታው ከተገኘ በኋላ፤ ባለሥልጣናቱ በሕይወት የተረፉ አለመኖራቸውን በሚያሳዝን ሁኔታ መረጋገጡን በመግለጫ ገልፀዋል።
