የኢትዮጵያ ወጣቶችና መጪው 7ኛው አገራዊ ምርጫ፡ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ፣ የሰላም ግንባታ እና የነገዋን ሀገር የመቅረጽ ኃላፊነት መግቢያ

Date:

መግቢያ


ግዮን መጽሔት :- ኢትዮጵያ በረጅም እና ውስብስብ የታሪክ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈች፣ አሁንም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሽግግር ሒደቶችን በማስተናገድ ላይ የምትገኝ ታላቅ ሀገር ናት፡፡

ሀገራችን ወደ 7ኛው አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ እየተቃረበች ባለችበት በዚህ ወሳኝ ታሪካዊ ምዕራፍ፣ የፖለቲካው ሒደት ማዕከላዊ ሞተር እና የሕዝቧ አብዛኛው ክፍል የሆኑት ወጣቶች የሚያደርጉት ተሳትፎ የሀገሪቱን የነገ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ትልቅ ትርጉም አለው። ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕያው ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው ዜጎች፣ በተለይም ወጣቶች፣ በንቃት ሲሳተፉበትና የሥርዓቱ ባለቤት ሲሆኑ ብቻ ነው።


ይህ መጪው 7ኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር ይበልጥ ለማስፋት፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ልዩ አጋጣሚን ይፈጥራል። በመሆኑም፣ ወጣቶች ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

የምርጫ ሒደት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማዕዘን ድንጋይ እንደመሆኑ መጠን፣ ወጣቱ ትውልድ በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት፣ በግጭት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ የነገዋን ኢትዮጵያ የመቅረጽ አደራ ተጥሎበታል። ይህ ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች በመጪው ምርጫ ተሳትፏቸው ሊጫወቱት ስለሚገባው ገንቢና ኃላፊነት የተሞላበት ሚና፣ እንዲሁም ምርጫው ለሀገር ግንባታ ያለውን ሰፊ ፋይዳ ለመዳሰስ በወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን (Youth and Cultural Development Foundation – YCDF) ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።


ወቅታዊ ምርጫዎች እና ዴሞክራሲያዊ ሰላም


በዘመናዊ የፖለቲካ ፅንሰ ሐሳብ እና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ፣ ወቅታዊ እና መደበኛ ምርጫዎች (Periodic Elections) ያላቸው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው። ምርጫ ዴሞክራሲን በተግባር የምንተረጉምበት፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት እና መንግሥታዊ ሥልጣን ሕጋዊ መሠረት የሚያገኝበት ቁልፍ መሣሪያ ነው።

መደበኛ ምርጫዎች በሀገር ግንባታ ውስጥ በርካታ መሠረታዊ ሚናዎችን ይጫወታሉ፤ ከእነዚህም መካከል ፖለቲካዊ ተጠያቂነት፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፣ የዜጎች ተሳትፎ እና የሕጋዊነት ማረጋገጥ ዋነኞቹ ናቸው።


አንደኛ፣ ፖለቲካዊ ተጠያቂነትን (Political accountability) ማስፈን የምርጫ ዐቢይ ግብ ነው። መደበኛ ምርጫዎች ዜጎች በሀገራቸው የአስተዳደር ሒደት ላይ በቀጥታ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ፣ እንዲሁም መንግሥታዊ አሠራሮች ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው እንዲሆኑ ያስችላሉ።

በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች የሕዝብን አደራ በአግባቡ ከተወጡ በድምፅ መስጫ ሳጥን ይሸለማሉ፤ ካልሆነም በሌላ የተሻለ ሐሳብ ባለው አካል ይተካሉ። ይህ ሒደት ፖለቲከኞች ሁልጊዜም ለሕዝብ ፍላጎት ተገዢ እንዲሆኑ ያስገድዳል።


ሁለተኛ፣ ምርጫ የፖለቲካ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚሸጋገርበት ወይም የሕዝብ ውክልና ዳግም የሚታደስበት (Peaceful transfer or renewal of political authority) የሠለጠነ መንገድ ነው። በፖለቲካዊ ታሪካችን ሥልጣን በአመጽ፣ በጦርነት እና በመፈንቅለ መንግሥት ሲለዋወጥ ያስከተለውን ሀገራዊ መከራ እና የሕይወት መጥፋት ጠንቅቀን እናውቃለን።

ወቅታዊ ምርጫዎች ይህንን አዙሪት በመስበር፣ የፖለቲካ ፉክክር ከጦር ሜዳ ወደ የምርጫ ክርክር መድረክ እንዲሸጋገር ያደርጋሉ። የፖለቲካ ልዩነቶች በአመጽና በጉልበት ሳይሆን፣ በሕዝብ የድምፅ መስጫ ሳጥን በኩል እልባት ሲያገኙ፣ ዴሞክራሲያዊ ሰላም (Democratic peace) ይረጋገጣል።


ሦስተኛ፣ የምርጫ ሒደት የዜጎችን ቀጥተኛ እና ንቁ ተሳትፎ (Citizen participation in governance) ያረጋግጣል። ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሰጪ መሆናቸውን በተግባር የሚያዩበት መድረክ ነው። በተለይም የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድምፃቸውን የሚያሰሙበት እና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የሚያስቀይሩበት ጉልበት ይሰጣቸዋል።


አራተኛ፣ መደበኛ ምርጫዎች ለፖለቲካዊ መረጋጋት እና ለሥርዓቱ ሕጋዊነት (Political stability, legitimacy, and peace) ያላቸው አስተዋጽዖ ወደር የለውም። አንድ መንግሥት ጠንካራ እና የተረጋጋ የሚሆነው በሕዝብ ነፃ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የሕጋዊነት ይሁንታ (Legitimacy) ሲኖረው ነው።

ሕጋዊነት ያለው መንግሥት ሀገራዊ ቀውሶችን ለመቋቋም፣ ሰላምን ለማስፈን እና ልማትን ለማፋጠን የሚያስችል የሞራል እና የፖለቲካ አቅም ይኖረዋል። በመሆኑም፣ 7ኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ሰላም መሠረት ለማጽናት፣ የፖለቲካ ተቋማትን ለማጎልበት እና ሀገራዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።


የኢትዮጵያ ወጣቶች በመንግሥት ግንባታና ፖለቲካዊ ሽግግር ውስጥ ያላቸው ታሪካዊ ሚና


የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን በጥልቀት ስንቃኝ፣ ወጣቶች በመንግሥት ግንባታም ሆነ በመንግሥት መፍረስ (Making and unmaking of the state) ውስጥ ተጫውተውት የነበረውን እና እየተጫወቱ ያለውን ጉልህ ሚና እንገነዘባለን። የኢትዮጵያ ወጣቶች የፖለቲካ ታሪክ ተመልካችቶች ሳይሆይ፣ ታሪክ ሠሪዎች ናቸው።


ከ1950ዎቹ አጋማሽ እና ከ1960ዎቹ ታዋቂው የተማሪዎች እንቅስቃሴ (Student movements and political activism) ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜው የፖለቲካ ለውጥ እና መዋቅራዊ የለውጥ ጥያቄዎች (Reform movements) ድረስ፣ ወጣቶች የፖለቲካ ንቃት ፈጣሪዎችና የለውጥ አንቀሳቃሾች በመሆን ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። አፋኝ ሥርዓቶችን በመገዳደር፣ ኋላቀር አሠራሮችን በማጋለጥ እና አዳዲስ የፖለቲካ ትርክቶችን በማስተዋወቅ ረገድ የኢትዮጵያ ወጣቶች የለውጥ እና የትራንስፎርሜሽን ሞተር (Drivers of transformation) ሆነው አገልግለዋል።


ይሁንና፣ ይህ ታሪካዊ ሚና ባለ ሁለት ስለት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። የወጣቶች የፖለቲካ ንቅናቄ ሁልጊዜም አዎንታዊ ውጤት ብቻ አላመጣም። የወጣቶች ኃይል በተገቢው መንገድ ካልተመራ፣ በስሜታዊነት ከተዋጠ፣ እና በጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያነት ሲወድቅ፣ አገራዊ አለመረጋጋትን ብሎም የመንግሥት መዋቅር መፍረስን (State unmaking) ሊያስከትል እንደሚችል ታሪካችን በግልጽ ያስተምረናል።

በ1960ዎቹ የተነሳው የለውጥ ኃይል ለርስ በርስ መናቆር እና መተላለቅ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩ፣ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት የወጣቶች ንቅናቄ ወደ አመጽ፣ ንብረት ውድመት እና የዜጎች መፈናቀል ማምራቱ የዚህ አሉታዊ ገጽታ ማሳያዎች ናቸው። ወጣቶች የፖለቲካ ልሂቃን መሣሪያ ሲሆኑ፣ ሀገር የማፍረስ አደጋን ሊያፋጥኑ ይችላሉ።


ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች በመጪው ምርጫ ይህንን ታሪካዊ እውነታ በሚገባ በመገንዘብ፣ አፍራሽ ከሆኑ አካሄዶች በመቆጠብ ኃይላቸውን ሀገር ለማፍረስ ሳይሆን የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባትና መንግሥታዊ ተቋማትን ለማደስ (Agents of renewal) ሊጠቀሙበት ይገባል። የትላንት ስህተቶችን ባለመድገም፣ የለውጥ ጥያቄዎችን በሠለጠነ የዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አግባብ ማቅረብ የዚህ ዘመን ወጣት ታሪካዊ ግዴታ ነው።

የዚህን ቀጣይ ፁሑፍ ነገ ይጠብቁን።

ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን (Youth and Cultural Development Foundation – YCDF) ከ UNDP ጋር በመተባበር ነው። የወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ውስጥ የወጣቶችን ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት፣ ባህላዊ እሴቶችን በማሳደግ፣ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በማስፋፋት እና የወጣቶችን ንቁ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በማጎልበት ላይ በትኩረት የሚሠራ ገለልተኛ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ግንዛቤ በመፍጠርና አቅማቸውን በማጎልበት የላቀ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአዳዲስ እና የሁለተኛ ዙር መራጮች አቅምና ሚና

ግዮን መጽሔት :- በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የአዳዲስ (ለመጀመሪያ...

በ’ፊንቴክ’ የማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩት ላይ ተጨማሪ ቀጠሮ ተሰጠ

በ"ፊንቴክ" ኢንቨስትመንት ስም በተፈጸመ  የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር...

የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት የኢንቨስመንት መጠን 723 ሚሊዮን ዩሮ መድረሱ ተሰማ

ከ20 በላይ የጣሊያን ኩባንያዎች  በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን...

የቴሌግራም ማስጠንቀቂያ

ቴሌግራም (Telegram) ኦፊሴላዊ ያልሆኑ የቴሌግራም መተግበሪያዎችን (Unofficial Apps) በሚጠቀሙ...