‹‹ማንም ሰው ጋር ጠባሳ መተው አልፈልግም››አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ

Date:

ግዮን መጽሔት :- ውድ የግዮን መጽሔት አንባብያን፣ በቅርቡ በሕይወተ ሥጋ ያጣነው ተወዳጁ አርቲስት ነጻነት ወርቅነት፣ በሙያው ተወዳጅ እየኾነ በመጣባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታን አድርጎ ነበር፡፡

የግዮን መጽሔት ታላቅ እህት ከነበረችው ‹‹ሐምራዊ›› መጽሔት 3ኛ ዓመት ቁጥር 23 ዕትም ጋር በሰኔ 2001 ዓ.ም ያደረገውን ይኽንን ቆይታ በወቅቱ በመጽሔቷ የሰፈረውን መግቢያ በማካተት የተወሰነውን ክፍል ለማስታወሻነት እንድታነቡት፣ ከነጻነት የጥበብ ጉዞ ታሪክ ጋር አያይዘን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

በተለምዶ በተለምዶ ኡራኤል ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡… በዚህ ወቅት ስኬታማ እየሆኑ ከመጡ ወጣት ተዋንያን መሃል አንዱ የሆነው ነፃነት ወርቅነህ በልጅነቱ በጣም ቀልደኛ ነበር፡፡ እናቱ እንጀራ ሲጋግሩ፤ ማጀት ጉድ ጉድ ሲሉ የሚለብሱትን ቀሚስ እያደረገ ቤት ውስጥ በሚያቀርባቸው አዝናኝ ቀልድ መላ ቤተሰቡ በሳቅ ማዕበል ይናወጣል፡፡


ከእሱ በዕድሜ የሚበልጡና በተለያዩ ክበባት የተደራጁ አማተር አርቲስቶች በአነስተኛ ፍራንክ በት/ቤቶች እየተዘዋወሩ ትያትሮችን ሲያሳዩ ትንሹ ነፃነት ሣንቲም ከፍሎ ላለመግባት ሲል ሁሌም የትኬት ሽያጭ ግንባር ቀደም አስተባባሪ ነው፡፡… እነሆ አሁን ደግሞ ሌላ ጊዜ ሆኖ ብዙዎች እሱን ለመመልክት ወረፋ መቆማቸው ግድ ሆኗል፡፡


በተለይም በዳዊት እንዚራ ትያትር ከብዙኃኑ ሕብረተሰብ ጋር ለመተዋወቅ የበቃው ነፃነት ወርቅነህ በዚህ ወቅት ተወዳጅ ለመሆን የበቃው የፍሬሽ ማን ትያትር ደራሲና አዘጋጅ ብሎም ተዋናይነው፡፡.. ዕድል ሀያ ትያትር በፊልም መልክ ተሠርቶ በቪሲዲ ሲወጣ ምርጥ ብቃቱን ያሳየው ይህ ወጣት ከምን ተነስቶ የት እንደደረሰ የሚያሳየውን የአብሮነት ቆይታችንን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡


ሐምራዊ፦ ትወናን በልጅነትህ ትመኘው ነበር?


ነፃነት- ይመስለኛል፡፡… የት/ቤት እና የሠፈር ጓደኞቼ የማደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች በጣም ያዝናናቸው ነበር፡፡ ያኔ መቼም ወደፊት ተዋናይ መሆን አልተመኘሁም ነበር ብልህ ውሸት ነው፡፡.. በዚህ መልክ ወደ ቀበሌ ክበብ አመራሁ፡፡ በኋላም ዩኒቲ የትያትር ክበብን ተቀላቀልኩ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልኩ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡


ሐምራዊ፦ በቅርበት የሚያውቁህ ልጅ ሆነህ በጣም ተንኮለኛ እንደነበርክ ይናገራሉ፡፡


ነፃነት- ይታረምልኝ፡፡…(ሳቅ)… ተንኮለኛ እንኳን አልነበርኩም፡፡ ምናልባት የምሠራቸው ነገሮች አዝናኝ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለማሳቅ የማደርጋቸው ነገሮች ከተንኮለኛነት ፈርጀውኝ ክሆነ እቀበላለሁ፡፡… ቤት ውስጥ በማደርጋቸወ እንቅስቃሴዎች ታላላቅ ወንድሞቼ በጣም ይዝናናሉ፡፡… እናቴ ሁኔታዬ ቢገርማትም ትምህርቴን እንድገፋበት እንጂ ወደ ጥበብ ዓለም እንድገባ ፍላጐቱ አልነበራትም፡፡


ሐምራዊ – በትልቅ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራኸው የት ነበር?


ነፃነት፡- በትያትር ደረጃ የመጀመሪያው ሥራዬ የስርየት ፊልም ደራሲ ደረጄ ፍቅሩ የፃፈው የጓሮ ጌታ የሚል ትያትር ነው፡፡ ቦታው ራስ ቲያትር ነው፡፡… አቤት ያኔ የተሠማኝን ደስታ አትጠይቀኝ፡፡ በተወሠነ ደረጃም ቢሆን መሥራት እንደምችል የተገነዘብኩበት አጋጣሚ ነው፡፡ ከዛ በኋላ የይቅርታ ምሽትን ማዘጋጃ ቤት ሠራሁ፡፡ በቀጣይነት የብሩክታይት ስጦታና የዳዊት እንዚራን ሠራሁ፡፡ ቀስ በቀስ ፊቴን ወደ ቴሌቪዥን በማዞሬ በርካታ የቲቪ ድራማዎችን ሠርቻለሁ፤ ፅፌያለሁ፤ አዘጋጅቻለሁ፡፡


ሐምራዊ፦ «ካምፓስ» የተሠኘ የቪዲዮ ፊልም ላይም ሠርተሃል። ፊልሙ ከተቀረፀ ከረዥም ዓመታት በኋላ ነው ለሕዝብ ዕይታ የበቃው። በፊልሙ ቀረፃ ወቅትና ፊልሙ ከወጣ በኋላ ያለው የእናንተ ተክለ ሠውነት ፈፅሞ አይገናኝም።


ነፃነት፡- ልክ ነው፡፡… እኔ ብቻ ሳልሆን አብረውኝ የተወኑት ልጆች በሙሉ አሁን ላይ በጣም ነው ልዩነት ያለን፡፡ በዛ ላይ ፊልሙ በቪ.ኤች.ኤስ ካሜራ ነው የተቀረፀው፡፡ አሁን ካለው ቴክኖሎጂ ጋር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ግን ያዩት ስዎች በሙሉ ሥራው የተሠራበትን ጊዜ እያገናዘቡ መሆኑን ነግረውኛል፡፡


ሐምራዊ፦ በዛ ላይ ገንዘቡ ተበልቶ አልቋል፡፡


ነፃነት፡- እሱም አለ…(ሳቅ)… ሙልጭ አድርገህ አጣጥመህ ብሪቷን ከጨረስክ በኋላ ሠው በየመንገዱ ላይ አዲሱ ፊልምህን አየነው ሲሉህ ባዶ ኪስህን የጐሪጥ መመልከት ብቻ ነው፡፡


ሐምራዊ፡- የግል ስብዕናህ ምን ይመስላል?… ነፃነት መሳቅ መጫወት እንጂ ስሜቱን በግልፅ አይናገርም ይሉሃል።


ነፃነት- የሚሰማኝን እናገራለሁ፡፡ ሰዎችን በጣም ነው የምወደው፡፡ ሠው የምወደው ራሴን በጣም ስለምወድ ነው፡፡ እኔን እንዲያከብሩኝ ስለምፈልግ ሰዎችን አከብራለሁ፡፡… በምንም ነገር ገደቤን አልፌ ሰዎች ላይ አልደርስም፡፡ ስትሠራ ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ ነገር ግን ግጭቶች እንደሚያልፉ እርግጠኛ እሆናለሁ፡፡ ማንም ሠው ጋር ጠባሳ መተው አልፈልግም፡፡ በሥራህ ወይ ትጐዳለህ ወይ ታገኛለህ፡፡… ስለዚህ ከሰዎች ጋር ያለኝን ግንኘነት ላለማበላሸት ስል ነገሮችን ቀለል አድርጌ ማለፍ ነው የምፈልገው፡፡


ሐምራዊ- ስመሆኑ ከሴት ልጅ ውበት ምን ታደንቃስህ?
ሐምራዊ- ራዕይ ያላት ልጅ ደስ ትለኛለች፡፡ የሴት ልጅ ጥሩ ተስፋ ብርታት ነው፡፡ እናቴ በእኔ ትልቅ ተስፋ ነበራት፡፡ እናቴና አያቴ ናቸው ያሳደጉኝ፡፡ እናቴ በእኔ የነበራትን ተስፋ፤ አያቴም በእኔ የነበራትን ተስፋ አውቅ ነበር። ቆንጆ ራዕይና ተስፋ ያላት ሴት አደንቃለሁ፡፡ ከሴት ልጅ ጥንካሬ፣ እምነትና ተስፋን እናፍቃለሁ፡፡


ሐምራዊ፦ በአሁኑ ሰዓት ፍሬሽ ማን የተሰኘው ትያትርህ በጣም ተወዶልሀል። ደራሲም፤ አዘጋጅም፤ ተዋናይም ነህ፣ እዚህ ላይ ትንሽ ያበዛኸው አይመስልህም?


ነፃነት:- ምኑ ነው የሚበዛው ሥራ እኮ ነው፡፡
ሐምራዊ፦ አንድ ሠው ሁሉንም ነገር በሞኖፖል ከሚይዝ የሥራ ክፍፍል ቢኖር የተሻለ ነው ለማለት ፈልጌ ነው፡፡


ነፃነት፡- ሥራዎችን የተለያዩ ባለሙያዎች ቢሰሩት መልካም ነው፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ ሁሉንም ነገር አንድ ሠው ሊሠራው ከቻለ ማድነቅም ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ትክክለኛ አካሄድ ይሆናል፡፡ በተለያዩ ሰዎች መሥራት ሥራውን የበለጠ የተዋበ ያደርገዋል፡፡ አንድ ሠውም የተለያዩ ነገሮችን በጣም ደክሞበት ከሠራው የተሻለ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡


ሐምራዊ፦ ዕድል ወይም ዕጣ ፈንታ ለምንለው ነገር ያለህስ አመለካከት ምንድነው?


ነፃነት፡- እኔ ዕድል ገና ለገና ይገጥመኛል ብዬ ቁጭ ብዬ አልጠብቅም፡፡ ሁሉም ሠው የየራሱ ዕድል ይኖረዋል፡፡ ወደ ፊት አብዝተህ ስታስብ እኮ ራሱ ዕድልህን ይፈጥርልሃል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እንዲሁ ዝም ብለህ ጥሩ ዕድል ሊገጥምህ ይችላል፤ ግን በዛ ዕድል ካልተጠቀምክበት ዕድሜ ልክህን ስታለቅስ ትኖራለህ፤ ግን ዋናው ነገር መጣርና ራስህ ዕድልን መፍጠር ነው፡፡


ሐምራዊ- ገና ወደፊት ብዙ የምትሠራ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ባለው የህይወት ጉዞህ የሚቆጭህ ነገር አለ?


ነፃነት:- የተቆጨሁባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ግን መልስ ሰጥቻቸዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡… ከዚህ ውጭ በጣም የሚያስቆጨኝ ነገር ነው ካልኩ ከፈጣሪ ጋር መጣላት ይሆንብኛል፡፡ እናትና አባቴ በህይወት የሉም፤ በእኔ የነበራቸውን ተስፋ በደንብ ቢያዩት ደስ ይለኝ ነበር። ግን እዚህ ውስጥ ገብቼ ከተቆጨሁ ከፈጣሪ ጋር መጣላት ነው፡፡ ከመቆጨት ይልቅ ዘወትር መልፋትና መጣርን እመርጣለሁ፡፡


ሐምራዊ፦ ለእኔ እዚህ ደረጃ መድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል ብለህ የምታስባቸውን ሰዎች እንድታመሰገን ዕድሉን ልስጥህ?


ነፃነት- ከልጅነቴ ጀምሮ አይዞህ ያሉኝን በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡… ፍሬሽ ማንን አብረውኝ የሠሩትን ተዋንያን በሙሉ እንደማከብራቸውና እንደማመሰግናቸው በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡… የጄአዲ ፕሮሞሽን ባለቤትና የጠብታ መፅሄት አዘጋጇ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤልና ሻምበል ታደስ ወ/ገብርኤልን ከልቤ አመስግናቸዋለሁ፡፡ ጓደኞቼ እንየው ደቻሳን፣ ተሻለ ወርቁን፣ የሀገር ፍቅርሥራ አስኪያጅ መንበረ ታደሰን በጣም አመስግናለሁ።


ሐምራዊ፦ እንሠነባበት?
ነፃነት፡- ይቻላል፡፡
ሐምራዊ፦ ሠላም ቆየኝ፡፡


የአርቲስት ነፃነት ወርቅነህ የጥበብ ጉዞ


አዲስ አበባ ኡራኤል አካባቢ በ1975 ዓ.ም ተወልዶ ያደገው ነጻነት ወርቅነህ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ የሕይወት ጥሪውን ለይቶ በማወቅ ለሚወደው የትያትር እና ጥበብ ራሱን የሰጠ እና በዚህም ለከፍተኛ ደረጃ የደረሰ አርቲስት ነበር፡፡ ተዋናይ፣ ኮሜዲያን፣ የቴሌቭዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ በኢትዮጵያ የፊልም እና የቴሌቭዥን ታሪክ ውስጥ የራሱን ልዩ የሆነ የአቀራረብ ስልት እና የትወና ጥበብ በማሳየት የሚታወቅ ባለሙያ ነበር፡፡


ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ የራሱን ትያትር በመድረስ እና ሴት ገጸ ባሕሪን ወከሎ በመተውን ጭምር ተሰጣኦውን ያሳየው አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ይህን ችሎታውን በጠዋት የተረዱት የአማርኛ መምህሩ ቲቸር ተሻለ ካበረታቱት በኋላ በቲያትር ሙያ እንደገፋበት በተለያዩ መድረኮች ተናግሮ ነበር፡፡


በዩኒቨርሲቲ የትያትር ክፍል ቆይታውም ከመምህራኑ ልዩ ድጋፍና አድናቆት የሚቸረው የያኔው ወጣት አርቲስት ነጻነት እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ሙያውን ለማሻሻል የሚጥር ድንቅ አርቲስት እንደሆነ የሙያ አጋሮቹ ይመሰከራሉ፡፡


የኪነ-ጥበብ አጀማመር ሲናገር እንደሚሰማው ነፃነት ወደ ጥበቡ ዓለም የገባው ገና በወጣትነቱ ሲሆን፣ በተለይም በኮሜዲ ስራዎቹ የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችሏል፡፡ ከሰራቸው ሥራዎች መካከል ፍሬሽ ማን፤ ያንቺው ሌባ፤ ኤፍቢአይ፤ ባለቀለም ህልሞች ይጠቀሳሉ፡፡


ነፃነት በተለይ የቴሌቭዥን ኢንዱስትሪን ከተቀላቀለ በኋላ ሥራዎቹ በኢቢኤስ (EBS) ቴሌቭዥን ላይ ‹‹የቤተሰብ ጨዋታ›› የተሰኘውን እጅግ ተወዳጅ ፕሮግራም ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን ሲያዘጋጅ እና ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ይህ የቤተሰብ ጨዋታ ፕሮግራም በተለይ ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነት ያስገኘለት ሲሆን ከህጻን እስከ አዋቂ የፕሮግራሙ አድናቂ ብቻ ሳይሆን በግንባር እና በየቤቱ ተሳታፊ የሆነበት ነው፡፡


ነጻነት በጥያቄ እና መልሶች አጋጣሚ ድንገት የሚፈጥራቸው ቀልዶች በእጀጉ ሳቅን የሚያጭሩ ናቸው፡፡ ይህ ፕሮግራም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲኖረው የእርሱ ጨዋነት የተሞላበት አቀራረብ እና ቀልድ ትልቅ ድርሻ ነበረው።


ሌላው ቀርቶ በተለየ የንባብ አቀራረብ የሚሰራቸው ማስታወቂያዎች በሌሎች ያልታዩ ልዩ መታወቂዎቹ ነበሩ።


ነጻነት በስብዕና በሥራ ባልደረቦቹ ዘንድ ተውዳጅ ሲሆን በትህትናው፣ ለሥራ ባለው ትጋት እና ሁልጊዜም ሰውን ለማስደሰት ባለው ዝግጁነት የሚወደድ እንደሆነ መላው የሥራ ባልደረቦቹ ይመሰክሩለታል።
የብቸኝነት ጉዞ እና ያልተሳካው ኑዛዜ የነፃነት ህይወት ገና በልጅነቱ ነበር በትልቅ ፈተና የተጀመረው፡፡ እናትና አባቱን ገና በለጋነቱ አጥቶ በብቸኝነትና በናፍቆት ያደገው ነፃነት፣ የልጅነት እጦቱን በኪነ-ጥበብና በሰው ፍቅር ለመካስ የጣረ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ ወላጆቹን ቢያጣም፣ እንደ እናትም እንደ አባትም ሆነው ያሳደጉትን አያቱን እጅግ ይወድና ያከብር ነበር፡፡


ለቅርብ ወዳጆቹ ደጋግሞ የሚናገረው አንድ ልብ የሚነካ ኑዛዜ ነበረው፦ “ስሞት ከአያቴ አጠገብ አሌልቱ ጊዮርጊስ ቅበሩኝ” የሚል፡፡ ይህ ምኞቱ ከአፈር በታችም ቢሆን አብሯቸው የመሆን ጉጉቱን የሚያሳይ ነበር። የሚገርመውና ልብን የሚሰብረው ግን፣ ነፃነት ከመሞቱ ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ አሌልቱ ጊዮርጊስ ተጉዞ ቤተክርስቲያኑን ስለማደስና ስለ ልማት ስራዎች ሲመክር መቆየቱ ነው። ሞት በደጃፉ እንዳለ ሳያውቅ፣ ለአያቱ ጓሮና ለዘላለም እረፍቱ ሲዘጋጅ የቆየ ይመስላል። ሆኖም የሀገር ዕዳና የጥበብ ባለቤት በመሆኑ፣ ኑዛዜው ሳይፈጸም የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በታላቁ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲሆን ተወስኗል፡፡


የመጨረሻዎቹ ሰዓታት እና የመሪር ጩኸት ድምፆች
ያቺ ጥር 8 ቀን የጥበብ ቤተሰብን ያረገደች መርዶ ይዛ መጣች። ነፃነት ለወትሮው የስራ እንቅስቃሴው ለመውጣት እየተዘጋጀ፣ ልብሱን እየለባበሰ ሳለ ድንገተኛ ህመም ተሰማው። ወደ ጓደኛው ደውሎ “አልቻልኩም” ሲል የነገረው የመጨረሻ ቃሉ ነበር። ህመሙ እየበረታ ሄዶ፣ ያ ሁሉ ፈገግታ፣ ያ ሁሉ የጥበብ ሀብትና ያ ሁሉ የወደፊት ተስፋ ከዚህ ዓለም ተለየ፡፡


ነፃነት ወርቅነህ፣ ከንፁህ ዘር በላይ ጋር ትዳር የመሠረተ ሲሆን የሦስት ልጆች አባት ነው። ልጆቹም የ18፤15 እና የ9 አመት ዕድሜ ሲኖራቸው የመጀመሪያ ልጁ ኦራገን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ እየተማረ እንደሆነ፣ ሁለተኛ ልጁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መከታተል እንደጀመረች እንዲሁም የመጨረሻዋ ለፒያኖ ፍቅር እንዳለት ከወራት በፊት ገልፆ ነበር፡፡


ነፃነት ወርቅነህ ጥር 8 ቀን 2018 ዓ.ም 44 ዓመቱን ሊይዝ 30 ቀናት ሲቀረው ከዚህ አለም ድካም አርፏል፡፡ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱም እሁድ፣ ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡


የግዮን መጽሔትና ኢትዮ ሐበሻ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹና መላው አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...

ትራምፕ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር...