የማያናማር ዋና ከተማ አቅራቢ በምትገኘውና የሀገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ማንዳላይ ግዛት በደረሰው ከባድ የርዕደ መሬት አደጋ፤ ቢያንስ ከ1 ሺሕ 2 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የሀገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በተጨማሪም በአደጋው 2 ሺሕ 376 የሚጠጉ ሰዎች መቁሰላቸውን ወታደራዊ ጦሩ ይፋ አድርጓል።
አደጋው እንደ መንገድ፣ ድልድይ እና ሕንጻዎች ያሉ መሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ በተጨማሪም በበርካታ ሰዎች ላይ ሕልፈት እና የአካል ጉዳት አስከትሏል።
በተጨማሪም በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ (ከምያንማር ዋና ከተማ 1 ሺሕ ኪ.ሜ ርቀት ላይ) በደረሰ ሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ፤ 10 ያህል ሰዎች መሞታቸው የከተማዋ ገዥ ቻድቻርት ሲቲፑንት አረጋግጠዋል።
ገዢው በከተማዋ እስከ አሁን 10 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች የመደርመስ አደጋ እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል።
አክለውም “ለቱሪስቶች መዳረሻ በሆነው ቻቱቻክ ገበያ አቅራቢያ በሕንጻ ግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ 100 የሚደርሱ ሠራተኞች እስካሁን የገቡበት አልታወቀም” ብለዋል።
በመገንባት ላይ የነበረው ባለ 30 ፎቅ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ በአደጋው ተደርምሶ በሰከንዶች ውስጥ ወደ ፍርስራሽ መለወጡን ተከትሎ፤ ሕንጻ ውስጥ የነበሩ ሠራተኞችን ለመታደግ የነብስ አድን ሠራተኞች ከአርብ ዕለት ጀምሮ በፍለጋ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“እኛ ባለን አቅም የተቻለንን እያደረግን ነው ምክንያቱም እያንዳንዱ ሕይወት አስፈላጊ ነው” ያሉት ገዥው፤ “ቅድሚያ የምንሰጠው ሁሉንም ለማዳን በተቻለ ፍጥነት እርምጃዎችን መውሰድን ላይ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል አስታውቀዋል።
የባንኮክ ከተማ አስተዳደር በአደጋው ከ2 ሺሕ የሚበልጡ የጉዳት ሪፖርቶች መድረሳቸውን ተከትሎ፤ በከተማው ዙሪያ የሕንጻዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ከ100 በላይ መሐንዲሶችን እንደሚያሰማራ አስታውቋል።
ትናንት አርብ ከሰዓት በኋላ በማዕከላዊ ማያናማር ሳጌንግ ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 7 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ ሲሆን፤ ከደቂቃዎች በኋላም በሬክተር 6 ነጥብ 7 የተመዘገበ ዳግመኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል።
በአሁኑ ጊዜም በአደጋው በተጎዱ አካባቢዎች ላይ ሕይወት የማዳን እና አስክሬን የማፈላለግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል
የመሬት መንቀጥቀጡ በማይናማር እና ታይላንድ የሚገኙ በርካታ ሕንፃዎችን ያወደመ ሲሆን፤ በተጨማሪም ድልድዮችን በማፈራረሱ የመንገዶችን መዝጋትን አስከትሏል።
አሁንም በአደጋው የደረሰው ትክክለኛ ጉዳት ገና እንዳልወጣ ብዙዎች እየተናገሩ ይገኛል።
