የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሊገባደድ በተቃረበው በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ካቀደው አጠቃላይ የገቢ ግብ ውስጥ 63 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት እንዳልቻለ አስታወቀ፡፡
ቢሮው በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረው 45 ቢሊየን ብር ቢሆንም፣ መሰብሰብ የቻለው 16.6 ቢሊየን ብር (36.89 በመቶ) ብቻ በመሆኑ 28.4 ቢሊየን ብር ሳይሰበሰብ ቀርቷል፡፡
ቢሮው ሰኔ 14/2018 በከፍተኛ አመራሮቹ ባካሄደው የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ እንደገለጸው፣ በበጀት ዓመቱ የገቢ አሰባሰብን ጨምሮ ዝቅተኛ አፈፃፀም የተመዘገበባቸውን ተግባራት ለማካካስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
በዚህም መሠረት የተመዘገበውን ዝቅተኛ አፈፃፀም ለማካካስና የቀረውን የገቢ ግብ ለማሳካት የሚያስችል፣ በአመራሩ ልዩ ክትትልና ድጋፍ የሚመራ የዘጠና ቀን እቅድ ተነድፎ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
ይህ እስከ ጳጉሜ 5/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው የዘጠና ቀናት የማካካሻ እቅድ፤ ከመሬት ሊዝ ጨረታ፣ ከአገልግሎት ለውጥ፣ ከመብት ፈጠራና ይዞታ አገልግሎት፣ እንዲሁም በምደባ ከሚተላለፉ ቦታዎች የሚገኝ የሊዝ ቅድመ ክፍያን ጨምሮ ከተለያዩ የገቢ አማራጮች ከ17.34 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
