የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ኒውክሌር የታጠቀ የባህር ኃይል ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት የሚደግፍ አዲስ 5 ሺህ ቶን የሚመዝን “ካንግ ኮን” የተባለ የክሩዝ ሚሳኤል እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ሙከራዎች ላይ ምልከታ ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡
እንደ ኮሪያ ማዕከላዊ የዜና ኤጀንሲ ዘገባ፤ ኪም ጆንግ ኡን ስትራቴጂካዊ የመርከብ ሚሳኤል ሙከራን እና ካንግ ኮን የተባለውን ፀረ-ሰርጓጅ መርከብ እና የአየር መከላከያ ስርዓቶችን ገምግመዋል፡፡
ፒዮንግያንግ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ስትቀጥል የስትራቴጂካዊ የሆኑ ክሩዝ ሚሳኤል ሙከራዎቿን አጠናክራ ቀጥላለች ነው የተባለው፡፡
የሰሜን ኮሪያ መንግስት ለዓመታት የባለስቲክ ሚሳኤል ልማት ላይ ትኩረቱን ካደረገ በኃላ አሁን ላይ የባህር ኃይልን ማደራጀት ላይ አተኩሯል፡፡ በዚህም የኑክሌር ኃይል ያለው ሰርጓጅ መርከቦች ግንባታ ላይ ትኩረቱን አድርጓል ይላል ቲአርቲ ወርልድ በዘገባው፡፡
