ሩሲያ፣ ወደ ዩክሬኗ ከተማ ኦዴሳ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መርከብ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ።
ዩክሬን አየር ኃይል እንደገለጸው፣ በጊኒ ቢሳው ሰንደቅ ዓላማ የሚንቀሳቀሰው መርከብ በሩሲያ የክሩዝ ሚሳዔሎች የተመታው ትናንት እሁድ ነው። የደረሰው ጥቃት እሳት አስነስቷል።
ከእሁድ ምሽት አንስቶ መርከቡ ላይ የነበሩ ሰዎችን ለመታደግ እና ለማግኘት የነፍስ አድን ሥራ እየተከናወነ ነው። የዩክሬን የባሕር ወደቦች ባለሥልጣን ሰኞ ጠዋት ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ዘጠኝ ባሕረተኞች እንዲሁም ከካፒቴኖቹ አንዱ መገደላቸውን አስታውቋል።
ባለፉት ሳምንታት ኦዴሳ ግዛት ተከታታይ ጥቃቶችን አስተናግዷል። ሩሲያ ሐምሌ ላይ ብቻ በግዛቱ ላይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 28 ሰዎች መገደላቸውን የግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ ኦሌህ ኪፐር ሰኞ ዕለት ለዩክሬን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ የሚጓዙ የጭነት መርከቦች ላይ የምትፈጽማቸው ጥቃቶችን ጨምረዋል።
ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ ብዙ ሰዎች የሞቱበት፣ እሁድ ዕለት በጊኒ ቢሳው ሰንደቅ ዓላማ የሚንቀሳቀሰው መርከብ ላይ የተፈጸመው ነው።
ዓለም አቀፍ ባሕርተኞችን ይዘው በአብዛኛው በውጭ ሰንደቅ ዓላማ ሥር የሚንቀሳቀሱት እነዚህ የጭነት መርከቦች የሚጓዙት፣ ዩክሩን በቀራት ብቸኛ የኤክስፖርት ኮሪደር በኩል ነው። በሮማኒያ እና ቡልጋሪያ የባሕር ዳርቻዎች በኩል ከዩክሬን ወደ ቱርክ ያጓጉዛሉ።
የሩሲያ ሙሉ ወረራ ከተጀመረ አንስቶ ላለፈው ከአራት ዓመት ተኩል በላይ የሚሆን ጊዜ በጥቁር ባሕር ላይ የሚደረገው ውጊያ በአብዛኛው አሸናፊ የነበረበት አይደለም።
የሩሲያ ጦር አብዛኛውን የባሕር ዳርቻ በመቆጣጠሩ የዩክሬን መርከቦች በኦዴሳ ዙሪያ ወዳሉ አካባቢዎች ርቀው መጓዝ አይችሉም።
ይሁን እንጂ ዩክሬን የምትፈጽማቸው የድሮን ጥቃቶች ሩሲያ ወታደራዊ አቅሟን በጥቁር ባሕር ምሥራቃዊ ክፍል ከሚገኙ የባሕር ኃይል ካምፖች እንዳታንቀሳቅስ አድርጓታል።
ሩሲያ አሁን በዚህ ባሕር ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ያጠናከረችው፤ የውጭ አገር ኩባንያዎች የዩክሬን ምርቶችን እንዳይገዙ እና የጥቁር ባሕር መተላለፊያን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ እንደሆነ ይታመናል።
