ኦማን ከኢራን ጋር በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ የምታደርገው ንግግር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ስትገልጽ ቴህራን በበኩሏ ማንኛውም ስምምነት ወሽመጡን ወዲያውኑ እንዲከፈት ያደርጋል ማለት አይደለም ስትል አስጠነቀቀች።
ሁለቱ አገራት ቅዳሜ ዕለት የሚደረገው ንግግር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ቢገልጹም ስምምነት መቼ እንደሚደረስ ግን ግልጽ አላደረጉም።
የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመርከቦች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ንግግሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስጠንቅቋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ውይይቱ የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹ ቢሆንም የወሽመጡ ዳግም መከፈት ግን “በሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው” ብለዋል።
ቴህራን አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ጥቃት ከፈጸሙባት በኋላ የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ በኦማን እና በኢራን መካከል እየተካሄዱ ያሉ ንግግሮች ያተኮሩት በወሽመጡ ውስጥ አዲስ የመርከቦች መንቀሳቀሻ መስመር መክፈት ላይ ነው።
በዚህ የባሕር መስመር ላይ ሁለቱም አገራት ኃላፊነት የሚኖራቸው ሲሆን ስምምነት ከተፈረመ መርከቦች ያለ ችግር መንቀሳቀስ እንዲችሉ ያደርጋል ተብሏል።
ነገር ግን አራጋቺ የወሽመጡ ዳግም ሙሉ በሙሉ መከፈት የሚወሰነው ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው ብለዋል።
እነዚያ ቅድመ ሁኔታዎች ምን መሆናቸውን በሚመለከት ግን የሰጡት አጭር ማብራሪያ ብቻ ነው።
አራጋቺ አሜሪካ በሰኔ ወር የተደረሰውን ስምምነት በመጣሷ ካሳ መክፈል ይኖርባታል ብለዋል።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሰኔ ወር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ወዲያውኑ የፈረሰ ሲሆን ዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችም ተቋርጠው ለቀናት የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ ቆይቷል።
የኢራን የደህንነት ኃላፊ ሞሐማድ ባጋር ዞልቃድር ደግሞ በሌላ መግለጫ ላይ አሜሪካ ባህሪዎን “እስክታስተካክል ድረስ” የሆርሙዝ ወሽመጥ አይከፈትም ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም አሜሪካ ስድስት የኢራን ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለባት ካሉ በኋላ ኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት እና ዛቻ ማቆም፣ ወደቦቿ ላይ የጣለችውን እገዳ ማንሳት፣ የታገዱ የኢራን ሃብቶች መልቀቅ እንደሚገኙባቸው ጠቅሰዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከኢራን ጋር “በቅርቡ” ስምምነት ይደረሳል ብለው የነበረ ቢሆንም ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ግን ቅዳሜ ዕለት የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ በመግለጽ ጥርጣሬያቸውን ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
BBC
