አገራቸውን በልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊነቶች ያገለገሉት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የፊታችን ቅዳሜ ነሐሴ 16 2018 በዳላስ ቴክሳስ በተደረገው የአርአያ ሰው ሽልማት ላይ ተገኝተው እውቅናቸውን ተቀብለዋል ።
በዕለቱ ሌሎች ለአገራቸው የሠሩ ኢትዮጵያዊያን የተሸለሙና መታሰቢያ የተደረግላቸው ሲሆን ከእነዚህ 9 ኢትዮጵያዊያን ኮሎኔል ጎሹ አንዱ ናቸው።
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ “የኮሎኔል ካሳ ገብረማሪያም መታሰቢያ ሽልማት” ተሸላሚ ሲሆኑ ይህም እውቅና ትልቅ የህሊና እርካታ እንደፈጠረላቸው ከተወዳጅ ሚድያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ነሐሴ 14 2018 በስልክ ከተወዳጅ ሚድያ መሥራች እዝራ እጅጉ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዕውቅናውን በማግኘታቸው ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ገልፀው ተወዳጅ ሚድያ የሚሠራውን የስነዳ ፕሮጀክት አድንቀው ትልቅ ሥራ መሆኑን መስክረዋል። የአርአያ ሰው ተብለው እጅግ በሚያከብሯቸው በኮሎኔል ካሳ ስም የተሰየመውን ሽልማት በማግኘታቸውም የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልፀዋል።
ሽልማቱ መታሰቢያ የተደረገላቸው ኮሎኔል ካሣ ገብረማርያም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ ኃይልና የኢትዮጵያን አየር መንገድ የበረራ ደኅንነትን መሥርተው በመምራት የሚታወቁ ነበሩ። የ 9ኛ ብርጌድ የሆለታ ገነት የጦር ት/ቤት የምዕራብ ዕዝና የ503ኛ ግብረ ኃይልን በአዛዥነት መርተዋል።
በመጨረሻም ናፍቃን ለማስለቀቅ በተሰጣቸው የሮራ ፀሊም ልዩ ግዳጅ ላይ እራሳቸውን በራሳቸው ለአገር ለወገናቸውና ለሰንደቃቸው ሲሉ በክብር የሰዉ የቁርጥ ቀን መሪ ከፍተኛ መኮንን ነበሩ።
ቅዳሜ ይህን የመታሰቢያ ሽልማት በክብር የሚበረከትላቸው ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በ1934 ዓ.ም በኤሊባቡር ክፍለ- ሃገር በጎሬ ከተማ ተወልደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው በማጠናቀቅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮተቤ ቀኃሥ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንደተማሩ ተወዳጅ ሚድያ የታሪክ ቋት ላይ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ፣ከ1951 እስከ 1954 ዓ.ም በሐረር ቀኃሥ ጦር አካዳሚ የ2ኛ ኮርስ የእጩ መኮንነት ትምህርታቸውን እንደተከታተሉም ታውቋል።
ኮሎኔል ጎሹ፣ ኮንጎ በመዝመት የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ግዴታቸውን ተወጥተዋል።በሐረር ጦር አካዳሚ በአሰልጣኝነት ተመድበውም ለ3 አመታት አገልግለዋል።
በማሪን አመራርና አደረጃጀት ሠልጥነው እንደተመለሱ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል አካል የነበረውን የማሪን ኮማንዶ ጦር አሠልጥነው አደራጅተዋል።
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ የቻንስለር ሜዳልያ በማግኘት ተመርቀዋል። በአሜሪካ በተካሄደ ኢንተርናሽናል የህግ ተማሪዎች ውድድር ( በመካፈል ቡድናቸው ከአሸናፊዎቹ ለመሆን ሲበቃ ኮ/ል ጎሹ ወልዴ በግላቸው ደግሞ ከጠቅላላ የውድድሩ ተሳታፊዎች መሃል ምርጥ ተናጋሪ ተብለው በመመረጥ ልዩ የዋንጫ ሽልማት አግኝተዋል።
በአሜሪካን ሃገር የሕግ ት/ቤቶች የእርከን አቀማመጥ መጀመሪያ ደረጃ ላይ ከሆነው የየል ዩኒቭርሲቲ በህግ የማስተርስ ዲግሪአቸውን በማዕረግ አግኝተዋል።
በ1969 ዓ/ም የሱማሊያ ወራሪን ለመከላከል ሚሊሻው በሚሰለጥንበት ወቅት በማሠልጠንና በአስተዳደር መኮንንነት አገራቸውን አገልግለዋል። ወደ ሶቭየት ኅብረት በማቅናትም በፍሩንዜ ሚሊታሪ አካዳሚ የአዛዥነትና ስትራቴጂ ትምህርት በመከታተል እውቀታቸውን አዳብረው በመመለስ በሠራዊቱ የተለያዩ ሃላፊነቶች ተመድበው አገልግለዋል።
ወደ ሲቪል ከፍተኛ የሥራ መደብ ተዛውረውም አገራቸውን በትምህርት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች በሚኒስቴርነት በብቃት አገልግለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን
እንደገና በማዋቀርና ሥርአተ ትምህርቱንም በአዲስ መልክ እንዲስተካከልም አድርገዋል።
በሚኒስቴርነት ኃላፊነታቸው ላይ የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ጉባኤና የብሔራዊ መሠረተ ትምህርት ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆነው በመምራት ከባድ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።አገር አቀፍ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ንድፈ ሃሳቡን በማፍለቅ፣ በማቋቋምና በመምራት ለዘመቻውም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አስተማሪዎችን በማሠማራት ጎልማሶችን ከመሃይምነት ቀንበር እንዲላቀቁ አድርገዋል። ይህም ለአገራችን በተባበሩት መንግሥታት (ዩኔስኮ) እውቅናና ሽልማት አስገኝቶላታል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ከ1983 እስከ 1986 ዓ/ም እአአ) በነበሩበት ጊዜ
በገለልተኛ መንግሥታና በአፍሪካ አንድነት መድረኮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች እንዲከበሩ ከፍተኛ ዲፕሎማስያዊ ትግል አካሄደዋል።
በወቅቱ በአገራችን በተከሰተው ርሃብ ከእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጎን በመሰለፍ የምግብ እርዳታዎች ከዓለም ዙሪያ እንዲሰባሰቡና ለተጎዱት ወገኖቻችን እንዲደርሱ ኮሎኔል ጎሹ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ኮ/ል ጎሹ ወልዴ በአሜሪካ የስደት ሕይወታቸው “የኢትዮጵያ መድህን ዲሞክራስያዊ ፓርቲ”ን መሥርተዋል።
በተለይም በ1991 ዓ/ም እአአ ሻእቢያና ኢሕአዴግ በወታደራዊ ኃይል አዲስ አበባና አሥመራን በተቆጣጠሩበት ማግሥት በአሜሪካን ሴኔትና ኮንግረስ ምክር ቤቶች በመገኘት አገዛዞቹ ሕዝባዊና ሕጋዊ ቅቡልነት እንዳያገኙ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል።
“የሰላምና የዲሞክራሲ ጉባኤ” በሚል ሽፋን በተዘጋጀው ስብሰባ የኤርትራን መገንጠል አስመልክቶ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ሕጋዊ ተቀባይነት እንደሌላቸው በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ 5ኛው ኮሚቴ ስብስባ ላይ በመገኘት ሞግተዋል ።
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በእውቀትና ልምድ የተካኑ፣ በዲሲፕሊን የታነጹ፣ የረጋና የማይዋልል በመርህና (ፕሪንሲፕል) በፍትህ የጸና ጠንካራ አቋም ይዘው የታገሉ ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው ጥቂት ብርቅዬ ልጆች አንዱ እንደሆኑ የአርአያ ሰው ሽልማት ፋውንዴሽን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ስለሆነም ለዘንድሮው (እአአ2026 ዓ/ም) የጀግናው ኮሎኔል ካሣ ገብረ ማርያም መታሰቢያ ሽልማት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴን ስንመርጣቸው በታላቅ አክብሮት፣ ደስታና ኩራት ነው ሲል የሽልማት ድርጅቱ ለኮሎኔል ጎሹ ያለውን ልዩ አክብሮት ገልጿል።
(ከዕዝራ እጅጉ)
