ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለሊዮ 14ኛ ሊቀ ጳጳስ የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቅዱስነታቸው ለሊዮ 14ኛ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሊዮ 14ኛ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ በመሆን በመመረጣቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም ገልጸው፤ “እንኳን ደስ አለዎ ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል።
የምድራችን ችግር በልዩ ልዩ ፈተናዎች እየጨመረ የመጣ መሆኑን የጠቆሙት አቡነ ማትያስ፥ “በእግዚአብሔር ኃይል የተመረጡ ሰዎችና መሪዎች ችግሮቹን በቀላሉ ማሸነፍ እና ፍሬ ማፍራት ስለሚችሉ፤ ቅዱስነትዎ ፈተናዎችን በሙሉ በቀላሉ በማለፍ የቤተ ክርስቲያንዎን ተልእኮ በላቀ ስኬት እንደሚወጡ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
አያይዘውም፥ “በአገልግሎትዎ ሁሉ እግዚአብሔር አምላክ ከጎንዎ እንዲሆን እመኛለሁ” ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
