የኮሜሳ ሴት ስራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ባዛር ለኢትዮጵያውያን ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የተሻለ የገበያ ትስስር እየፈጠረ ነው

Date:

የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) የሴት ሥራ ፈጣሪዎች ንግድ ትርዒት ለኢትዮጵያውያን ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የተሻለ የገበያ ትስስር እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ።

የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) 21 አባል ሀገራት ከ600 ሚሊዮን በላይ የህዝብ ቁጥር እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርታቸውም ከ760 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑንና ይህም ሰፊ የገበያ ዕድል እንዳለው የሚያሳይ ነው።

ኮሜሳ በአፍሪካ ትልቁና ሰፊው ቀጣናዊ የጋራ ገበያ ሲሆን በስሩ 14 የተለያዩ ተቋማትን ይዟል።

ከተቋማቱ አንዱ የሆነው የኮሜሳ ሴት ነጋዴዎች ፌዴሬሽን ሲሆን በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል።

ኢትዮጵያ በዚሁ ተቋም የተዘጋጀውን 6ኛውን የኮሜሳ ሴት ስራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ባዛር እያስተናገደች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት በረከት ወርቁ ለኢዜአ እንዳሉት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ሴቶች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበትን መድረክ ማመቻቸት ይገባል።

ለሴት ስራ ፈጣሪዎች ትኩረት ተደርጎ ከትላንት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የንግድ ትርዒትና ባዛር ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን ሴት ስራ ፈጣሪዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ማስተዋወቃቸውን ነው የገለጹት።

በዚህም በተለያዩ ክልሎች ያሉ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ከኢትዮጵያ አልፎ ለአለም ገበያ መቅረብ የሚችሉ ተወዳዳሪ ምርቶችን የማምረት አቅም እንዳላቸው ያስመሰከሩበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ሴት ስራ ፈጣሪዎች በኮሜሳ አባል ሀገራት ውስጥ የገበያ ዕድላቸውን እንዲያሰፉና የቢዝነስ ስምምነቶችን እንዲፈጽሙ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ሴቶች በቀላሉ የንግድ ስራ ላይ እንዳይሰማሩ ከሚያደርጉ ተግዳሮቶች ውስጥ የፋይናንስ አቅርቦትና የቴክኖሎጂ እጥረት ይጠቀሳሉ።

በተለይም የፋይናንስ አቅርቦቱን ችግር ለመፍታት የፋይናንስ ተቋማት ሴቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ የብድር አማራጮችን ያመቻቻሉ።

የእናት ባንክ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አክሊል ግርማ ባንኩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የብድር አማራጮችን ማቅረቡን ይናገራሉ።

ይህም ሴቶች የንግድ ስራቸውን በቀላሉ እንዲያስፋፉና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ያግዛል ብለዋል።

የንግድ ትርዒቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ የባዛሩ ተሳታፊ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ናቸው።

ከንግድ ትርዒትና ባዛሩ ተሳታፊዎች መካከል አስተያየታቸውን የሰጠችው ከጀበና ቡና ንግድ ተነስታ አሁን ላይ የካፌና ሬስቶራንት ባለቤት የሆነችውና ቡና ላይ እሴት ጨምራ ለገበያ እያቀረበች የምትገኘው ብጽዕት ዮሴፍ አንዷ ናት።

ስራ ፈጣሪዋ እንዳለችው ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ ውጪ በተካሄደው የሴት ስራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒት ላይ በመሳተፏ በርካታ ልምዶችን ከማግኘት ባለፈ ምርቶቿን መሸጥ ችላለች።

የተለያዩ ዕቃ መያዣ ምርቶችን በማምረት ለገበያ የምታቀርበው ሰላም ሞገስ በበኩሏ የንግድ ትርዒቱ ጥሬ ዕቃዎችን ለማግኘትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያግዛል ነው ያለችው።

በሻማ ምርት ስራ ላይ የተሰማራችው ህይወት ተፈራ እና በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርት ላይ የተሰማራቸው ኤደን ሃይሉ የንግድ ትርዒቱ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና የገበያ መዳረሻቸውን እንዲያሰፉ ማስቻሉን ያነሳሉ።

ከትላንት ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የኮሜሳ ሴት ስራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ባዛር ከ400 በላይ የኮሜሳ አባል ሀገራት ሴት ስራ ፈጣሪዎች የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶቻቸውን አቅርበዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...

ከ 50 ሚሊዮን በላይ መራጮች በማንዋልና በዲጂታል ተመዝግበዋል

ከየካቲት 28_መጋቢት 28 የመራጮች ምዝገባ ሲካሄድ እንደነበር ይታወቃል። በተለያዩ ጉዳዮች...