‹‹ከፍታ ድንግዝግዝ ለዋጠው ሕይወቴ ብርሃን ፈንጥቋል››

Date:

ሕይወት ደሳለኝ

ሕይወት ደሳለኝ ትባላለች፡፡ ልክ እንደ ሥሟ የሕይወቷን ፈተናዎች በጽናትና በቆራጥነት ተጋፍጣ፣ ችግርን ወደስኬት መቀየር የመቻል አንፀባራቂ ምሣሌ የኾነች እንስት ናት። ሕይወት ገና በ25 ዓመት ዕድሜዋ ነበር ያለባትን የአካል ጉዳት ተቋቁማ ትምህርቷን ለመቀጠል በመወሰን በአካውንቲንግ በዲፕሎማ መርኃ ግብር በተሳካ ሁኔታ ለመመረቅ የበቃችው። እንዲህ ባለ ብርታት ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ሕይወት ግን፣ የሥራ እድል በማግኘት ረገድ ችግሮች አጋጠሟት፡፡ በዚህም ሳቢያ የድህረ ምረቃው የሕይወት ምዕራፏ ፈታኝ ኾነ።

ሕይወት ጥሩ የትምህርት ውጤት ቢኖራትም፣ በሥራ እድል መጥፋት እና ባመለከተችባቸው ቦታዎችም ምላሽ ባለማግኘቷ ተስፋ ለመቁረጥ ተገደደች። በተጨማሪም በተወዳደረችባቸው የሥራ መስኮች የሥራ ልምድ እና ተጨማሪ ልዩ ክህሎቶችን መጠየቋ፣ ከዚያ ቀደም ምንም ዐይነት የሥራ ልምድ ላልነበራት ተመራቂዋ ሕይወት ተግዳሮቶቿ የበለጠ የተባባሱ መስሎ እንዲሰማት አደረገ። እነዚህ ገጠመኞች ሲደማመሩም ሕይወት ‹‹ሕይወቷን›› ለመለወጥ ባላት ተስፋ ላይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲያልባት ምክንያት ኾነ።

በድንገት ግን ድንግዝግዝ የዋጠው የመሰለው ሕይወቷ የተስፋ ብርሃን ብልጭ አለበት፡፡ ይኽ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀው ደግሞ በዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን ሥር ስለሚተገበረው የከፍታ ለወጣቶች ፕሮጀክት በማወቋ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ወጣቶችን በሕይወት ክህሎት፣ በውሳጣዊ ክህሎት ብሎም በሥራ እድል ፈጠራ ጭምር ሥልጠና የሚሰጥበት መኾኑ ደግሞ ተስፋ በመቁረጥ አለንጋ እየተገረፈች ለነበረችው ሕይወት ትልቅ ዕድል ነበር። ሕይወት ጊዜ ሳታባክን በደስታ ነበር፣ በሻሸመኔ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን አስተባባሪነት የሚሰጠውን የወጣቶች ከፍታ ፕሮጀክት የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና ፕሮግራምን የተቀላቀለችው።

ሕይወት በከፍታ ወጣቶች ፕሮጀክት የሚሰጠውን የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተጠቅማ በለውጥ ጉዞ ውስጥ ለመራመድ አንድ ወር ጊዜ ነበር ያስፈለጋት። ሥልጠናው አስተሳሰቧን ከመቀየር ባለፈ የሥራ ገበያን በምን መንገድ መፍጠር እንደምትችል ብሎም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወቷን ለማጎልበት የሚያስችላትን በዋጋ የማይተመን ክህሎት አስታጥቋታል። ሕይወት እንደማንኛውም ሰው ብቃቷን በተግባር ለመተርጎምም ኾነ ምኞቷን ለማሳካት የሚያስችል ዐቅም እንዳላት ስትረዳ ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜቷ በከፍተኛ ሁኔታ አየለ። የአጭር እና የረዥም ጊዜ ግቦችን ያካተተ የግል የዕድገት እቅድ ነድፋም የስኬት ፍኖተ ካርታዋ አደረገች።

ዛሬ ላይ ሕይወት የወጣቶች ከፍታ ፕሮጀክት ፍሬ ከመኾን አልፋ የዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን ሥልጠና አስተባባሪ ኾና ለመቆም ያስቻላት ቁመና ላይ ተሰይማለች፡፡የተጠቀሱት ፕሮጀክቶች የማይናወጥ ድጋፍ፣ የአመለካከት ለውጥ ሥልጠና እና ክህሎት በራሷ እና በሙያዋ ላይ ላመጣችው የለውጥና እድገት ጉዞ አጋዥ ኾነዋታል። ሕይወት ትናንት ያጋጠሟትን ፈተናዎች በድል ከማሸነፍ አልፋ ነገዋ ያማረና የተሣካ ይኾንላት ዘንድ አሁን የምትገኝበትን ክህሎት እና አስተሳሰብ እንድትጨብጥ ላደረጓት የከፍታ ወጣቶች ፕሮጀክትም ኾነ ለዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን እንዲሁም የሥልጠና አስተባባሪዋ ልባዊ ምሥጋናዋን ታቀርባለች። ሕይወት አሁን ላይ በተላበሰችው የራስ መተማመን እና ቁርጠኝነትም፣ ምንም ዐይነት እንቅፋት ሳይበግራት ወደ ተሣካ የሕይወት ጎዳና ለመጓዝ በተጠንቀቅ ቆማለች።

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 219 ሕዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ስኩል 20ኛ ዓመት ክብረ በዓል

ዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ስኩል 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ...

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ20 አትሌቶች  የማስጠንቀቂያ አውጥቷል

በውድድሩ ላይ ያልተገኛችሁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይመለከታል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓለምአቀፍ...

የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር፤ ለወረራ የታለመ ማደናገሪያ? ሩሲያ ማስጠንቀቂያ ሰጠች!

በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ውጥረትን ለመቀነስ...

“ሕገ መንግሥቱ መገንጠልን ይፈቅዳል ፤ ሕዝቡ ደግሞ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ዋጋ ይከፍላል”

አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል(የ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› መጽሐፍ ደራሲ) ግዮን መጽሔት :-...