“  IMF፣ ብድር ለመስጠት ይህን አባልነት እንደ ቅድመ ሁኔታ ይጠቀምበታል ”  አቶ ክቡር ገና

Date:



ኢትዮጵያ የአለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከ1996 ጀምሮ፣ ላለፉት 20 አመታት እየተደራደረች ትገኛለች፡፡

እስካሁን ድረስ ከተቋሙ ጋር አምስት ዙር ድርድሮች የተደረጉ ሲሆን፣ በተለይ በቅርቡ በስዊዘርላንድ፣ ጄኔቫ የተደረገው አምስተኛው ድርድር መልካም ውጤት የተገኘበት እንደሆነ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

ኢትዮጵያ፣ የሚጠበቅባትን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት በሚቀጥለው አመት የአለም ንግድ ድርጅት ሙሉ አባል እንደምትሆንም ተገልጿል።

ለመሆኑ የአለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን የሚያስገኘው ጥቅም ምንድነው ? ፣ ሀገራት የድርጅቱ አባል ሲሆኑ ምን ያገኛሉ ፣ ምንስ ያጣሉ ? በሚሉት ሐሳቦች ዙርያ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያን ጠይቀናል፡፡

ባለሙያው አቶ ክቡር ገና፣ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “ በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የነበረው ሒደት ያዝ ለቀቅ የበዛበት ነበር፣ አሁን ግን መንግስት ጠንከር ብሎ የገፋበት ይመስላል፣ ድርጅቱን ለመቀላቀልም ጫፍ ላይ ተደርሶዋል ” ብለዋል፡፡ 

አቶ ክቡር ገና፣ ድርጅቱን ለመቀላቀል የሚጠየቁትን ቅድመ ሁኔታዎች አብራርተዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያው ምን አሉ ?

“ ድርጅቱን ያቋቋሙት እና ቀድመው የተቀላቀሉ ሀገራት፣ ያስቀመጡዋቸው ህጎችና ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ወደ ድርጅቱ የሚመጡ ሀገራ እነዛን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ የዚህ ድርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው ድርድር ሒደት፣ የድርጅቱ አባላት እና በኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ያገባኛል የሚል ሀገር ሁሉ ጥያቄውን ያቀርባል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ግን፣ የአንድ ሀገር የንግድ ዘርፍ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መደረግ አለበት የሚል ነው፡፡

የአለም ንግድ ድርጅት ዋና አለማ፣ የሀገሪቱ ሀብት ለውጭ ባለሀብቶች ተስተካክሎ እንዲቀርብ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ፋይናንስና ቴሌኮሚኒኬሽን ያሉ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች እንዲከፈቱ ያስገድዳል፡፡ እዛ ድርጅት ውስጥ ሲገባ የፖሊሲ ለውጥ መደረጉ አይቀርም፡፡ ከአለም ንግድ ድርጅት ህግጋትና ደንቦች ጋር የሚጣጣም ፖሊሲ ይወጣል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም በዚህ በኩል የፖሊሲ ማስተካከያ ያደርጋል፡፡

የአለም ንግድ ድርጅት ውስጥ መግባት ማለት ስምምነትን መቀበል ማለት ነው፣ ከአለም ንግድ ድርጅት አሰራር ጋር የሚጣጣም ፖሊሲ ብቻ ነው ማውጣት የምትችለው፡፡ እንደፈለጉ ፖሊሲ ማውጣትና መቀያየር ያበቃል፡፡ ”

ለአባል ሀገራቱ ምን ጥቅም ያመጣል፣ ኢትዮጵያስ ምን ትጠቀማለች ? 

“ የኢትዮጵያ ገበያ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሲደረግ፣ ለውጭ ምርቶች የቀረጥ ቅነሳ ይደረጋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶች አሁን ከሚጣልባቸው ቀረጥ ባነሰ መጠን ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ በዚህም ሸማቹ ይጠቀማል፣ እነዛን ምርቶች ዝቅ ባለ ዋጋ ይገዛቸዋል፡፡

በሌላ በኩል የመንግስት ገቢ ይቀንሳል፡፡ ቀድሞ ከፍተኛ ቀረጥ በማስከፈል ያገኘው የነበረው ገቢ ይቀንስበታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ስለሚበዛ፣ በአለምአቀፍ የጥራት ደረጃ ያልተመረተ ምርት ተወዳዳሪ አይሆንም፡፡

የድርጅቱ አባል ሲኮን፣ የሌሎች ሀገራት ምርቶች ቀድሞ ከነበረው ቀረጥ ባነሰ መጠን ይገባሉ፡፡ በዚህ ጊዜ፣ ምርታቸውን በአለም አቀፍ የጥራት ደረጃ የማያመርቱ የኢትዮጵያ ድርጅቶች በሙሉ ከባድ ፈተና ላይ ይወድቃሉ፡፡ በተለይ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ከባድ ውድድር ሊገጥማቸው እንደሚችል አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የምርትቻው ጥራት አለምአቀፋዊ ደረጃን ያልጠበቀ ከሆነ፣ ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡

የሀገር ውስጥ አምራቾች እስከዛሬ ድረስ በቀረጥ ጥበቃ ሲደረግላቸው ቆይተዋል፡፡ ቀረጥ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ከለላ የሚሰጥበት አሰራር ነው፡፡ የድርጅት አባል ስትሆን ግን፣ ይህ ከለላ ይቀራል፡፡ ”

ምን ያህል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል ?

“ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ስንወስን፣ ቀድመው መከናወን የሚገባቸው ስራዎች ነበሩ፡፡ ቀድሞ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ እና አምራች ዘርፉን መደገፍ ይገባ ነበር፡፡ በዚህ በኩል ጥያቄ አለኝ፣ ብዙ አልተሰራም ብዬ ነው የማስበው፡፡ የሀገር ውስጥ አምራቾች አቅማቸው እንዲዳብርና ለውድድር እንዲዘጋጁ አልተደረጉም፡፡ ይህ ባለመደረጉ፣ አባልነቱ አሁን ያሉትን ድርጅቶች ያዳክማቸዋል፡፡

ለአባልነቱ የሚደረገው ንግግር እና ውይይትም በአብዛኛው የመንግስት ሐላፊዎችን ብቻ ያካተተ ነው፡፡ የንግዱ ማህበረሰብና መሪዎቹ፣ የአለም ንግድ ድርጅትን ከመቀላቀል ጋራ ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው ችግር በትክክል ምን እንደሆነ አላስቀመጡም፡፡ በድርድሩ እንኳን መሳተፍ ባይቻል፣ ቀድሞ መደረግ ስላለበት ነገር ግን ሀሳብ መስጠት ይቻል ነበር፡፡ ”

ድሆች ሀገራት ከዚህ ድርጅት ይጠቀማሉ ?

“ የሚጠቀሙ ሀገራት ይኖራሉ፣ ግን ምን ያህል ናቸው፣ በምን ዘርፍ ነው የተጠቀሙት የሚለው መታየት አለበት፡፡ በአብዛኛው ግን ተጠቅመዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ከአፍሪካ ሀገራት የሚፈለገው እርሻ ምርታቸውንና የማዕድን ሀብታቸውን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ድርጅቱ ድጋፍ ይሰጣል፡፡

የሀገራቱ ህዝብ ከድህነት እንዲወጣና የተሻለ ህይወት እንዲኖረው ማድረግ የሚለው ግን የአለም ንግድ ድርጅት አሰራር ውስጥ ቦታ የለውም፡፡

ውጤቱ ይህ ከሆነ፣ የነዚህ ሀገራት መንግስታት ለምን አባል መሆን ይፈልጋሉ ለሚለው ጥያቄ፣ መልሱ ተፅዕኖ ስለሚደረግባቸው ነው፡፡

የዛ ድርጅት አባል መሆን፣ ሌሎች የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ ለመግባት ይጠቅማል፣ አለምአቀፍ ንግድ ላይ አለመስማማት ካለ፣ በድርጅቱ በኩል የሚታይበት ሁኔታ ይኖራል፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ይስባል፣ የሚሉ ምክንያቶችም ይቀርባሉ፡፡

የአለም ንግድ ድርጅት ግልፅ አሰራር እንዳለው አድርጎ ነው ራሱን የሚያቀርበው፣ የድሆቹን ሀገራት ሀሳብ እንደሚሰማም ይገልፃል፡፡ በተግባር ሲታይ ግን እንደዛ አይደለም፡፡ ወደዛ ለመግባት አለምአቀፉ የገንዘብ ተቋምም ያስገድዳል፡፡

IMF ብድር ለመስጠት የዚህን ድርጅት አባልነት እንደ ቅድመ ሁኔታ ያቀርቦዋል፡፡ ከእኔ ብድር መውሰድ ከፈለጋችኹ፣ አንዱ ማሟላት ያለባችሁ ቅድመ ሁኔታ፣ የአለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ነው ይላቸዋል፡፡ ”

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...