አሜሪካ በሁቲ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ባለው የሰሜን ምዕራብ የየመን ክፍል ውስጥ አፍሪካውያን ስደተኞች ተይዘው በሚገኙበት ማዕከል ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 68 ሰዎች መገደላቸውን የታጣቂ ቡድኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
አል ማሲራህ የተባለው የሁቲ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዳለው ሳአዳ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ማዕከል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከሞቱት በተጨማሪ አብዛኞቹ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 47 ሰዎች ቆስለዋል።
ጣቢያው በአንድ የወደመ ሕንጻ ፍርስራሽ ሥር የተቀበሩ የበርካታ ሰዎች አስከሬኖችን የሚያሳይ አሰቃቂ ምሥሎችን አሳይቷል።
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በርካታ ስደተኞች አደገኛውን የቀይ ባሕር መስመርን በሕገወጥ መንገድ በማቋረጥ ወደ የመን እንሚገቡ ይታወቃል።
ስደተኞቹ በጦርነት በምትታመሰው የመን በኩል በማቋረጥ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና የባሕረ ሰላጤው አገራት ይጓዛሉ።
በዚህም በባሕር ላይ ጉዞ ከሚደርስባቸው አደጋ በተጨማሪ የመን ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ለጉዳት እንደሚጋለጡ ሱዘገብ ቆይቷል።
በአሜሪካ ጥቃት በስደተኞች ማቆያ ላይ ደረሰ ስለተባለው ጉዳት ከአሜሪካ ጦር ሠራዊት በኩል ወዲያውኑ የተሰጠ ምላሽ የለም።
