‹‹ማኅበራዊ ሚዲያ በደመነፍስ ለሚሰጥ መፈራገጥ እንጂ ችግሮችን በወጉ ተንትኖ ምላሽ መስጫ መድረክ አይደለም››
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
እንዴት ሰነበታችሁልኝ ወዳጆቼ!
ባለፈው ወር አንዳርጋቸው ፅጌን ለንደን ላይ እንዳገኘሁትና ከሱ ጋር ያደረኩትን ውይይት እንደወረደ አቅርቤላችሁ ነበር፡፡ ብዙዎቻችሁ ለሰጠችሁኝ ገንቢ አስተያየት ክብር ይስጥልኝ፡፡ ዛሬ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ሲዘገጃጅ እንደተለመደው ስልክ ደውሎ ‹‹ነገ ማታ ወደ ሐገሬ ስለምጓዝ ልሰናበትህ ነው›› አለኝ፡፡ በመገረም ‹‹እርግጠኛ ነህ?!›› አልኩት፡፡ ሞቅ ባለ ሞራል ‹‹እርግጠኛ ነኝ!!›› አለና ቀጠለ፡፡
‹‹እንደነገርኩህ የመጣሁበትን ጉዳዮቼን ከሞላ ጎደል ጨርሻለሁ፡፡ ስለዚህ መቆየቴ ምን ትርጉም አለው?›› አለኝ፡፡ ውሳኔው ቢያስደስተኝም ለጨዋታው ድምቀትና ለውይይታችን መነሻ እንዲሆን አንድ ጥያቄ መዘዝኩ፡፡
‹‹እንደምትሰማው ሀገር ውስጥ ከፍተኛ ችግር አለ›› አልኩት፡፡
‹‹እሱማ ፀሐይ የሞቀው ዓለም ያወቀው ነው፡፡ ምኑን ትነግረኛለህ?›› በማለት ጨዋታውን ሊቀጥል ሲል ‹‹ለክፉ ለደጉም መጥቼ ልሰናበትህ እፈልጋለሁ›› በማለት ወደ አረፈበት መኖሪያ ቤት ገሰገስኩ፡፡
በመንገዴ ላይ ስለ ሐገሬ የሚያስጨንቁኝን ጉዳዮችና እርስ በእርስ ስለሚወነጃጀሉት ፖለቲከኞች ከእራሴ ጋር ሙግት ገጥሜ እያወጣሁና እያወረድኩ ነበር የተጓዝኩት፡፡
ምን ብናደርግ ይሻለናል? … መንግሥት ምክር ለመቀበል ዝግጁ አይደለም? … ለማዳመጥ የተቸገረበትን ምክንያት ሊገለጥልን አልቻለም? በዚሁ ከቀጠልን ሐገራችንን ከገባችበት ቅርቃር ውስጥ ፈልቅቆ ለማውጣት ገና ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ችግሮቻችን ውስብስብ እያሉ ነው፡፡ እኔ በጣም ስጋት ውስጥ ገብቻለሁ። አንዱን ጣራ ስንደፍን ሌላው ጣሪያ ያፈሳል፡፡ የችግራችን ሽንቁር ብዙ ነው፡፡ ሰላማዊ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባትም ሆነ ሰርቶ ማደር ተቸግረዋል፡፡ በአጠቃላይ የሰላም ዋስትና ጠፍቷል፡፡ በዚህ ምክንያት የኑሮ ውድነቱ፣ መፈናቀሉ የሕዝቡን ሕይወት ለማስቀጠል ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል።
ችግሩ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ነው። የሃይማኖት ቀውሱ ለግዜው ነው እንጂ ገና አልተፈታም፡፡ ዘረኝነቱ፣ የብሽሽቅ ፖለቲካውና የሰብዓዊ ቀውሱ ሐገራችንን ትልቅ ችግር ውስጥ ከቷታል፡፡ ሁሉም ችግሮቻችን ከኛ አቅም በላይ አይደሉም፡፡ ነገር ግን መደማመጥ አቃተን፡፡ ሁሉንም በጦርነት የምናስቆም እየመሰለን የሰላም አማራጭን ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ትተን የኃይል አማራጭን እንደመፍትሔ ወስደነዋል፡፡
‹‹ስለዚህ በነዚህ ጉዳዮች ላይ የአንተ አስተያየት መስማት እፈልጋለሁ›› ስል ውይይታችንን ከፈተኩት፡፡
ደግነቱ አንዳርጋቸው አንድን ነገር ለማስረዳት ውስብስብ አድርጎ ሳይሆን በድፍረት እና በራስ የመተማመን ሙሉ ብቃት ስላለው የምጠይቀውን ጥያቄዎች በአግባቡ እንደሚመልስልኝ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
መልሶቹ አጭርና ግልፅ በመሆናቸው ቁምነገሮቹን ተከታትሎ ለመሰብሰብ ከባድ አይሆንም፡፡ በዚህ ላይ በትምህርትና በልምድ የበሰለ ነው፡፡ እንደ አንዳንድ ፖለቲከኛ ፕሮፖጋንዲስቶች በተሽቀረቀሩ ቃላቶች ንግግሮችን አሳምሮ መልስ መስጠት አይፈልግም። በደንብ ያዳምጣል፣ ችግሮቹን በጥልቀትና በማስተዋል መርምሮ የማስረዳት አቅሙ ከብዙዎቹ ጉምቱ ፖለቲከኞች የተሻለ ነው፡፡ ምናልባት የፍልስፍና ተማሪም በመሆኑ የጥያቄዎቹን መነሻና መድረሻ መዝኖ አቅጣቻዎችን ከነመፍትሔው ስለሚያስቀምጣቸው ውይይታችን ከወዲሁ ተስፋን የሰነቀ ነበር።
እንደዘመኑ ፖለቲከኞች ብዙ ተረትና ምሳሌዎችን አይደረድርም፡፡ የኩረጃ ፖለቲካንም አጥብቆ ይጠላል፡፡ ‹‹መኮረጅ የቱንም ያህል ነባራዊውን ዓለም መለወጥ አይችልም›› የሚል የፀና አቋሙን በተደጋጋሚ ነግሮኛል፡፡
በተለያዩ ጊዚያቶች የተለያዩ አጀንዳዎች እያነሳሁ ካነጋገርኳቸው ፖለቲከኞች ውስጥ አንዳርጋቸው ፅጌ የራሱ የሆነ ጥሩ ስብዕና አለው፡፡ ሐብትና ገንዘብ፣ ዝናና ሥልጣን ለሱ ምኑም አይደሉም። ከቅርብ ጓደኞቹ እንደሰማሁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንዴም ሁለቴ ማንም ፖለቲከኛ በስለት ሆነ መቀመጫቸውን ስሞ የማያገኘውን ሥልጣን ‹‹ልስጥህ›› ብለውት ‹‹አሻፈረኝ›› ማለቱን ሰምቻለሁ። የሥልጣኖቹን ዐይነት ጠቅሼ ‹‹እውነት ይህን ሥልጣን አልፈልግም አልክ?›› ብዬ ጠይቄው ነበር። እሱም አልካደም። ‹‹ለምን?›› አልኩት። በወቅቱ የሰጠውን ምላሽ ነገረኝ።
‹‹የሃገሬ ሕዝብ ሁሉም ሰው ፖለቲካ ውስጥ የሚገባው ‹ሥልጣን ፍለጋ ነው› የሚል በምጸት የተሞላ አስተያየት አለው። እኔ የሃገሬ ሕዝብ ለነጻነት ብቻ የሚታገሉ ሥልጣን የማይፈልጉ ልጆች እንዳሉት እንዲያምን እፈልጋለሁ። ሥልጣን ወስጄ ይህን ምጸቱን ማጠናከር አልፈልግም ነው ያልኩት›› አለ፡፡
‹‹እንዲህ ዐይነቱን ነገር እኮ ሕዝብ አያውቅም። ማወቅ አለበት! ለምን እንዲያውቅ አላደረግክም? እኔ ይፋ ላድረገው?›› አልኩት።
‹‹ሕዝብማ ያውቃል፣ የትኛውም ሥልጣን ላይ እንዳልሆንኩ። እያወቀ እንደማያውቅ መስሎ ለሚያወራው የራሱ አጀንዳ ላለው የዩቲዩብ ሸቃይ የፌስቡክ አክቲቪስት ምላሽ መሥጠት አያስፈልግም። ብትመልስላቸውም ሰመተው አያቆሙም። ስለዚህ ተወው። አስፈላጊ በሆነ ሰዓት እኔው ራሴ እናገረዋለሁ›› አለኝ።
ይህ አንዳርጋቸውን ከስግብግብ የሥልጣን ናፋቂ ጓደኞቹ ልዩ ሰው ያደርገዋል፡፡ ያለ ምንም ማጋነን ለአንዳርጋቸው የአስተሳሰብ፣ የስሜት እና የባሕሪ መገለጫዎቹን ስንቶቻችን ጠንቅቀን እንደምናውቅ አላውቅም፡፡
በውይይታችን ወቅት አንዳርጋቸው የትኛውም ዐይነት ዘረኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥቅሉ፣ ወይም የአንድ ብሔርን ሕዝብ ከገባበት ችግርና ፈተና ያወጣል ብሎ እንደማያምን ደጋግሞ ነገሮኛል። ሆኖም ግን የሃገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዘረኝነትን ጨምሮ በማቃለል ትልቅ ድርሻ ያለው የሀገሪቱ መንግሥት ኃላፊነቱን በሚገባ ባልተወጣ ቁጥር ‹‹ተበድለንናል ፤ ተግፍተናል›› በሚል ቁጭት ወደ ብሔረተኛነት ወይም ዘረኛነት የሚሄዱ የትኛዎቹንም አካላት አላወግዝም። ሌሎችንም ችግሮች በተመለከተ እንደዚያው ነው። ዘረፋና ሌብነት የመንግሥት መገለጫ በሆነበት ሃገር ከመንግሥት ውጭ ያሉ ዘራፊዎችን በየትኛው የሞራል መመዘኛ ነው የማወግዘው? ወገንተኛ የሆነ ከሀገሪቱ እውነታ ጋር የማይገናኝ እጅ እጅ የሚል ፕሮፓጋንዳ በመንግሥት እጅ ያሉ ሚዲያዎች እያሰራጩ በምን ምክንያት ነው የግል ሚዲያዎች ዩቱዩበሮች የተጋነነ፣ እውነትነት የሌለው ዜና እና መረጃ ያሰራጫሉ ብዬ የምኮንናቸው። ሕዝብ በኑሮ ውድነት ሕይወት ሲኦል በሆነችበት ሃገር ከፍተኛ ወጪ እያወጣ በሰበብ አስባቡ ድግስ የሚደግስ መንግሥት ባላበት፣ በጣም የተቀናጣ ሕይወት የሚገፉ ባላስልጣናት ባሉበት ሃገር በምን አፌ ነው ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ባገኘው ሃብት አንድ ነጋዴ በ70 ሚሊዮን ብር ሰርግ ደገሰ ብዬ፣ ባለሃብቶቹን ኧረ ለከት ይኑራችሁ የምላቸው። ለኔ ሁሉ ነገር ተጀመሮ የሚያልቀው መንግሥት ላይ ነው። መንግሥት የተሻለ ሥራ ሲሰራ አርአያነት ሲያሳይ ከታች ያለው ሕዝብ ሲያስቸግረው እኔም ወገኖቼን ምነው ጎበዝ ለምን የማይበጅ ሥራ እንሰራለን ለማለት ድፍረቱን እናገኛለን። ከዛ ውጭ ግን በረጅም ሕይወቴ ጭፍን የአንድ ድርጀት ወይም መንግሥት ደጋፊ ሆኜ አላውቅም። በቀረችኝም እድሜ ከዚህ በፊት ያልነበረኝን ባሕል መላበስ አልችልም።
በዚህ ምክንያት አንዳርጋቸው ጽጌን የአንድ ብቸኛ አስተሳሰብ ድሀ ኾኖ አላገኘሁትም። የሰው ልጅ ብስለት የሚለካው ደግሞ በጅላጅል ጅላንፎ አስተሳሰብ ላይ ችክ በማለት ሳይሆን የተለያዩ አስተሳሰቦችን በብቃት ማስተናገድ መቻሉ ይመስለኛል።
ዘረኝነትን በማጦዝ አስተሳሰብን መገደብ የእውቀት በሮችን ሁሉ እንደሚቆልፍ አስቀድሞ ስለገባው በሐሳብ ልዩነት የሚያምን ሰው በመሆኑ አስደስቶኛል። ስለዚህ አዕምሮው ገሐዱን እውነታ በትክክል የተረዳ በመሆኑ ግምቴ ትክክል ከሆነ አንዳርጋቸው ፅጌ ከሕሊና ባርነት ነፃ ወጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ አስታውሳለሁ በአንድ ወቅት ውይይት ስናደርግ የሰዎችን ሐሳብ ሳንንቅ መቀበል እንደሚገባ በአፅንኦት ነግሮኛል፡፡ እሱ እንዳለው ብዙ አስተሳሰቦችን በመሰብስብ የሚገነባ አገር ደግሞ ጠንካራና በቀላሉ የማይናድ በመሆኑ አስተማማኝ ለውጥ ማምጣት ያስችላል፡፡
ሌላው ጥንካሬው ደካማና የተሸናፊነት ስሜት አይታይበትም፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለውጥ በኢትዮጵያ እንዲመጣና የወያኔ ሥርዓት ተንኮታኩቶ እንዲወድቅ ታላቅ ተጋድሎ ካደረጉት ፖለቲከኞች ውስጥ የመጀመሪያው መስመር ላይ ሥሙ የሚቀመጠው አንዳርጋቸው ፅጌ ነው። ከሐገር አገር እየተንከራተተ ከእንግሊዝ ሐገር ኤርትራ በርሀ ጦር ግንባር በመግባት ለወያኔ እራስ ምታት የሆነ ታጋይ ነበር። በመላው አውሮፓና አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና የአፍሪካ ሐገሮች እየተዘዋወረ ዳያስፖራው ሕብረተሰብን በመቀስቀስ የትጥቅ ትግሉን አምኖበት የመራና ግንቦት ሰባትን የፈጠረው አንዳርጋቸው ፅጌ ሲሆን የመን ላይ ታፍኖ እስር ቤት እስከ ተወረወረበት ግዜ ድረስ ለኢትዮጵያ ዋጋ ከፍሏል።
እንዳለ መታደል ሆኖ ውለታ ቢስ ትውልድ ላይ በመድረሳችን አሜሪካና ኢትዮጵያ ተቀምጦ ‹‹ትግሉን መርቼ ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ›› ሲሉን ‹‹አዎን›› ብለን በመቀበላችን የመጀመሪያውን ስህተት የሰራነው ያን ጊዜ ነው።
ወዳጆቼ እኔ ይህንን ያህል ከነግርኳችሁ ቀሪውን ራሱ አንዳርጋቼው ጽጌ ይግልፅላችዃል፡-
‹‹አለባቸው፣ ጥያቄዎችህን ከነማብራሪያው አዳምጫለሁ። ከኔ የምትፈልገው መልስ እውነት ወይንስ ሐሰት የሚል የምርጫ ጥያቄ አይመስለኝም፡፡ በእያንዳንዱ ጥያቄህ ውስጥ የሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ድምፅ ሲጮህ ይሰማኛል፡፡ እኔም እንደ አንድ ዜጋ ድምፃቸው ከፍ ብሎ እንዲስማ አብሪያቸው እጮሀለሁ፡፡ በቀላል ምሳሌ ላስረዳህ፡-
‹‹የራበው ሰው ሰርቆ ሲበላ ቢያዝ ተጠያቂው ሰርቆ የበላው ነው ወይንስ ያስራበው ሥርዓት? ነፃነትም እንደዚያው ነው። አንድ ሰው ዝም ብሎ አይሸፍትም፣ ጠመንጃ አንስቶ ለመፋለም ከተነሳ የነፃነት ረሀብ ይዞታል ማለት ነው። የፍትህ የነጻነትና የእኩልነት ረሃብ ከባድ ነው። ይህ ጠኔ ሲበዛ ሕዝብ ያምጻል። አየህ፣ ከዚህ በተረፈ ማንም ሰው ለሀገሩ አደጋ መሆን የሚፈልግ ያለ አይመስለኝም። ለሕዝቡ የምንሰጠው አጉል ተስፋ ትዝብትና ጥርጣሬ ላይ ከጣለን ተሸንፈናል ማለት ነው። ለውጥ ለናፈቀው ሰው ፍሬ የማይሰጥ ዛፍ እየተከልን የምናሳየው ከሆነ፣ ፍሬው ሲጠፋ ሌላ ፍሬ የሚሰጠው አማራጭ መፈለጉ የማይቀር ነው። የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነውና።
‹‹አሁን አንተ እንደጠየከኝ ብዙ ጋዜጠኞች ደጋግመው ሥጋታቸውን ጨምረው ይጠይቁኛል፡፡ መንግሥትን ጨምሮ ሁላችንም የመፍትሔው አካል ከመሆን ይልቅ የችግሩ ፈጣሪዎች እንሆናለን፡፡ እንደምትከታተለው በማኅበረሰቡ ዘንድ በእየለቱ የሚነሱ ብዙ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ተገቢው መልስ በተገቢ ጊዜ አልተሰጠም። ይህንን በመሳሰሉ ምክንያቶች ሕዝብ በከፍተኛ መስዋዕትነት ያመጣው ለውጥ ውርጃ ገጥሞታል ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እነዚህ ጥያቄዎች ወደድክም ጠላህም በመንግሥት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠራቸው የማይቀር ነው፡፡
‹‹ሕዝብን ዝም ብለህ ስትገፋው ጥያቄ በማንሳት ብቻ የሚያቆም ከመሰለህ ፖለቲካ ምን እንደሆነ ያልገባህ ጮርቃ ነህ ማለት ነው። ይህ ሕዝብ ምንም አያደርግም የሚል የሕዝብ ንቀት በዓለም ላይና በሃገራችንም በርካታ መንግሥታትን ለውርደት የዳረገ ነው።
‹‹ከሁሉም በላይ ለአንድ ሐገር ሕዝብ ሰላም መሠረታዊ ቁልፍ ጥያቄ ነው። እንደምታውቀው በአገራችን በአብዛኛዎቹ ክልሎች ማለት ይቻላል ሁከትና ብጥብጡ እየባሰበት እንጂ እየተረጋጋ አይደለም። በየቀኑ የሰው ሕይወት ይጠፋል፤ ሰው ይታገታል፣ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ተሰደዋል፣ ለብዙ ዓመት ያጠራቀሙት ሐብት ተዘርፏል፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተጥሰዋል፤ ሥነልቦናዊ ጫና ደርሶባቸዋል። በጥንት ዘመን የሰው ልጆች መንግሥትን የመሠረቱት፣ ግድብ እንዲገድብ፣ መንገድ እንዲሰራ፣ ትምህርት እንዲያስፋፋ፣ የጤና አገልግሎት እንዲያቀርብ አይደለም። እነዚህ ሁሉ የመንግሥት ሥራዎች በጣም ቆይተው የመጡ ናቸው። ሰዎች መንግሥትን የመሠረቱት ሕይወታቸውን፣ ንብረታቸውን እና ነጻነታቸውን እንዲንከባከብ ነው። ይህ ጥንት የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ነጻነታቸው ቀንሰው ለመንግሥት የሰጡት ሥልጣን ነው። ይህን ማድረግ የተሳነው መንግሥት ከመንግሥት ሊቆጠር የሚችልበትን ምክንያቶች ያጣ መንግሥት ነው።
‹‹በአጠቃላይ ሥርዓተ አልበኝነት የሀገራችን ሁኔታ ዋንኛ መገለጫ ወደሚሆንበት ዘመን እየተንደረደርን ነው፡፡ ሰው አፍኖ እና ሰውሮ ገንዘብ መጠየቅ፣ አፍኖ ወስዶ መደብደብ፣ ገድሎ መጣል፣ አስገድዶ መጥለፍ፣ የዜጎች መብት የሚገፋበት፣ የደህንነት ዋስትና የሌለበት ሐገር ሆነናል። ሕዝብ እንደዚህ ዐይነት ድርጊቶች ሆን ተብሎ ፖሊሲ ተዘጋጅቶላቸው የሚፈጸሙ እስኪመስለው ድረስ እየተፈጸሙ ነው። ሕዝብ ጉዳዮቹን ፖሊሲ ወጥቶላቸው የሚፈጸሙ ናቸው የሚል እምነት ላይ ያደረሰው የችግሮቹ ተቀጣጣይነት፣ መበራከትና መባዛት፣ በመንግሥት አካላት ጭምር የሚፈጸሙ መሆናቸው ነው።
‹‹በተደጋጋሚ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ጭፍን ደጋፊዎቻቸው መንግሥት ከሚሞክረው ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ሲናገሩ ታዳምጣለህ። መንግሥትን የሚቃወመው ኃይል አማራጮቹን በሚገባ አደራጅቶ በዝርዝር ማቅረብ ባለማቻሉ አማራጮች የሉም የሚሉትን የመንግሥት አካላትና ደጋፊዎች የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል። ይህ ማለት ግን የሃገሪቱን ችግሮች መቀነስ የሚችሉ መንግሥት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች የተሻሉ በርካታ አማራጮች የሉም ማለት አይደለም። አሉ። እነዚህ ግን በጥቂት የትዊተር መስመሮች ወይም የፌስ ቡክ ገጾች ወይም በአንድ ሰዓት የዩቲዩብ ውይይቶች በወጉ መቅረብ የማይችሉ ናቸው። ማኅበራዊ ሚዲያ በደመነፍስ ለሚሰጥ መፈራገጥ የተመቸ ሚዲያ እንጂ ዘለቂታዊ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በወጉ ተንትኖ በወጉ ምላሽ መስጫ መድረክ አይደለም። በርካታ ገጾች የሚወጣው የጥናት የምርምር ስራ የሚጠይቅ ነው። ጥናትና ምርምር ሲባል አገር ምጥ ላይ ሆና ዓመታትን የሚፈጅ የአካዳሚ ጥናት ማለቴ አይደለም። በፍጥነትና በርጋታ ከማስብ ጋር አገናኝቶ በጥድፊያ መቅረብ ያለባቸውን መፍትሄዎች ማቅረብ ነው።
‹‹የአንዳዶቹ ችግሮች መፍትሄ ጥናትና ምርምር የማይጠይቅ ከጠንካራ የፖለቲካ መንፈስና ቁርጠኛነት ጋር የተያያዘ ነው። ብዙ ችግሮች በዚህ መንገድ መፈታት ይችላሉ። አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው በርጋታ ማሰላስልን የሚጠይቁ። እኔ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በፌስቡክና በትዊተር ገጾች በሃገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሱ ማለቂያ የሌላቸውን በደሎች በየደቂቃው በማውገዘ የአክቲቪስት ሚና መጫዎት አልችልም። ባሕሪዬ አይፈቅድልኝም። ይህን ሥራ የሚሰሩ በርካታ ሰዎች አሉ። የጠፋው የሃገራችንን እና የሕዝባችንን ችግሮች በዘለቄታው እንዴት እንፈታለን የሚሉ ሥራዎች ላይ አተኩሮ የሚሰራ ነው። መንግሥት የችግሮች አባባሽ እንጂ የመፍትሔ አካል እየሆነ አይደለም። ተፎካካሪ ፓርቲዎች እየሰሩት አይደለም። አካዳሚያው እየሰራው አይደለም። እኔ የሚያስጨንቀኝ ይኼ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያመጡ የሚችሉ አካሄዶች በደንብ እያተስተዋልኩ ነው። አቅሜ ውስን ቢሆንም በዚህ ዘርፍ የተቻለኝ ለማድረግ እጥራለሁ።
‹‹ምናልባት ጥያቄዎችህን መልሼልህ ከሆነ በዚሁ ብናጠቃልል ምን ይመስልሀል?›› አለኝ፡፡ በእርግጥ ገና የሚቀሩኝ ሕዝብ ማወቅ የሚገባቸው ጥያቄዎች ነበሩኝ፡፡ ጊዜው እየሮጠበት ነው። ለጉዞ የሚሆኑ ዝግጅቶች እንደቀሩት ነግሮኛል። ስለዚህ እንዲህ በማለት ተሰናበትኩት። ‹‹የተባረከች ሌሊትና መልካም መንገድ ይሁንልህ!››
ወዳጆቼ እኔም በዚሁ አበቃሁ። በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን።
