ሂውማን ራይትስዎች የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች “በኢትዮጵያ ያለውን ቀውስ” ትኩረት እንዲሰጡበት አሳሰበ

Date:

ሂውማን ራይትስ ዎች በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉ የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ መሪዎች ባቀረበው ጥሪ፤ “በኢትዮጵያ እያሽቆለቆለ ባለው የሰብአዊ መብት አያያዝ እና በትግራይ ክልል ባለው ደካማ የሰላም ሁኔታ” ላይ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጠይቋል።

የመብት ተሟጋች ድርጅቱ በጥር ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ መካከለኛውና ደቡባዊ ክፍሎች በኢትዮጵያ ሠራዊትና በትግራይ ኃይሎች መካከል እንደገና የተቀሰቀሰው ግጭት ከፍተኛ መፈናቀል ማድረሱን ጠቁሟል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ባለፈው ሳምንት የካቲት 3 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት ማሳሰቢያ፣ በቀጣናው ያለው “አስከፊ የሰብአዊ መብትና ሰብአዊ ሁኔታ” ይበልጥ ሊባባስ እንደሚችል በመጥቀስ፣ የተፈጸሙ ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ መጠየቃቸውን ድርጅቱ አስታውሷል።

ሂውማን ራይትስ ዎች በአማራ ክልል የቀጠለውን ግጭት በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጎረቤት አገር ኤርትራ የታጠቁ ቡድኖችን እየረዳች ነው ሲሉ መክሰሳቸውን በዘገባው አካቷል።

ተቋሙ አክሎም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ መደፍረስ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ስጋት መሆኑን ገልጿል። ሂውማን ራይትስ ዎች የኅብረቱ መሪዎች ለሲቪሎች ጥበቃ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቋል።

ተቋሙ በህዳር 2015 ዓ.ም የተፈረመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የፈረሙም ሆኑ ያልፈረሙ አካላት ለሲቪሎች ጥበቃ እንዲያደርጉ፣ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን እንዲያረጋግጡ እና የሽግግር ፍትሕ እርምጃዎችን እንዲተገብሩ ተጽዕኖ እንዲደረግ ጠይቋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በስምምነቱ መሠረት ለተቋቋመው የአፍሪካ ኅብረት የክትትል ቡድን ተጨማሪ ታዛቢዎችን እንድትፈቅድ እንዲሁም የኅብረቱ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት የክትትል ዘዴውን የሰብአዊ መብት ጥበቃ አካል እንዲያጠናክር እና ስለሚፈጸሙ ጥሰቶች መደበኛ የሕዝብ ሪፖርት እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርቧል።

“በዚህ ጉባዔ ላይ ሪፖርት ማቅረብ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ማጠናከር፣ ተጨማሪ ጥሰቶችን ለመከላከል እና የሲቪሎችን ስቃይ ለማስቆም ወሳኝ ነው” ያለው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ “የምናባክነው ጊዜ ሊኖር አይገባም” ብሏል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...