የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ አሜሪካ የሚገኘው ሄኖክ አርጋው ፋውንዴሽን፣ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ 133 አይነት የተለያዩ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችንና የህክምና ግብአቶችን ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡
መሳሪያዎቹ ለኩላሊት፣ ለተኝቶ ታካሚዎች፣ ለፅኑ እና መደበኛ ሕሙማን ህክምና ግልጋሎት የሚያግዙ ናቸው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት፤ “ቸር ልብ ያላቸው እልፍ ዜጎች አሉን ፤ ከዲያስፖራ እስከ ሀገር ቤት ካላቸው የሚያካፍሉ፣ ከጎዶሎአቸው የሚሰጡ ፣ በመስጠት ውስጥ ያለን በረከት የተረዱ ፣ ለሀገሬ ምን አደረኩላት የሚሉ፣ ቸር፣ ሀብታም ልብ ያላቸዉ እልፍ ወንድም እህቶች አሉን።
ዛሬም በሀገረ አሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት የሚገኘው “ሄኖክ አርጋው ፋውንዴሽን” ዋጋቸው ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ 133 አይነት የተለያዩ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችንና የህክምና ግብአቶችን አበርክቶልናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሄኖክ አርጋው ፋውንዴሽንን በከተማ አስተዳደሩ፣ በተጠቃሚው ማህበረሰብና በራሴ ስም እጅግ አድርጌ እያመሰገንኩ፤ ድጋፉ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልም ለአስተዳደሩ የጤና ቢሮ አስረክበናል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
