የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ (Heart to Heart Children’s Aid) በማርዮት ሆቴል ዋሽንግተን ዲሲ ባከናወነው የማጠቃለያ መርሐግብር 350 ሺህ ዶላር ማሰባሰቡን የድርጅቱ መሥራች አቶ ብርሃን ተድላ አስታውቀዋል።
ከዚህ ውስጥ በቀጥታ በባንክ ገቢ የተደረገ 110 ሺ ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ቀሪው ቃል የተገባና በአጭር ጊዜያት የሚሰበሰብ መሆኑን አንስተዋል።
በተገኘው ገቢ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ በወረፋ ላይ ለሚገኙ 120 ሕጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ይሰጣል ተብሏል።
በተጨማሪም ኤፕሪል 24 ከጣሊያን በሚመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት ለተጨማሪ 50 ሕጻናት ሕክምና የሚሰጥ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በወራት ጊዜ ውስጥ የሕክምና ተጠቃሚዎች ቁጥር 170 ለማድረስ ታቅዷል።
ድርጅቱ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ በአራት የሀገሪቱ አካባቢዎች የልብ ቀዶ ጥገና ማእከላትን ለማቋቋም አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
በመርሐግብሩ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ወጣት አዶናይ ብርሃነ፣ ወ/ሮ ሀና ክብሩና ባለቤታቸው ሳሚ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
