በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተፈናቀሉ ዜጎች የተዋጣ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ አውጥተው ሊዘርፉ ሞክረዋል የተባሉ ሠራተኞች እና የሥራ ሃላፊዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ ፡፡
ሠራተኞቹ እና ሃላፊዎቹ የተያዙት ብሩን ከአዲስ አበባ ንግድ ባንክ ሸገር ቅርንጫፍ በቼክ ለማውጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ ባሉቡት ወቅት ነው ተብሏል ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ለግላቸው ሊያውሉት ነበር የተባለው 60, 276,383 (ስልሳ ሚልዮን ሁለት መቶ ሰባ ስድሰት ሺ ሶስት መቶ ሰማንያ ሦስት ብር ) ነው ፡፡
ገንዘቡ በዞኑ ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ከተለያዩ የህብረተብ ክፍሎች የተሰበሰበ ነው ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ብሩን ከባንክ ሊያወጡ የሞከሩት ቀደም ሲል ተሠርቶ ቮይድ የተደረገ / የተሠረዘ / የቼክ ቅጠልን በመጠቀም ነው ሲል የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት ለጎፋ ዞን አስተዳደር በደረሰው ጥቆማ መሠረት በተደረገ ክትትል መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡
የዞኑ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ብዛትም ሆነ የነበራቸውን የስራ ድርሻና ሃላፊነት በመግለጫው አልጠቀሰም ፡፡
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ዞኑ መንግሥት ኮሚኒኬሽን የሥራ ሃላፊ ቢደውልም በመግለጫው ከተጠቀሰው ውጭ የሚሰጡት ተጨማሪ መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል ፡፡
ይሁንእንጂ ቀጣይ የምርመራው ሂደት ሲጣራ ተከታትሎ የሚያሳውቅ መሆኑን ዞኑ በመግለጫው ጠቁሟል ፡፡
DW Amharic
