ላንድማርክ  ሆስፒታል “የዓለም የታካሚዎች ደህንነት ቀን” አከበረ

Date:

*በየዓመቱ ጥራቱና ደህንነቱን ባልተጠበቀ ህክምና በመላው ዓለም 3 ሚሊየን ዜጎች ሕይወታቸው ያልፋል።

*የህሙማን ደህንነት ቀን የሚከበርበት ዓላማ በህሙማን ደህንነት ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል ።

*”የምንሰጠው ህክምና የሚፈውስ እንጂ የሚጎዳ እንዳይሆን መትጋት ይገባል”

*የላንድ ማርክ አጠቃላይ ሆስፒታል ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ከሚሰጡና የህሙማንን ደህንነት ለማስጠበቅ ከሚሰሩ የግሉ ዘርፍ  ሆስፒታሎች አንዱ ነዉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ የሚከበረው “የዓለም የህሙማን ደህንነት ቀን” በላንድ ማርክ አጠቃላይ ሆስፒታል ለ5ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ተከበረ ።

ላንድማርክ አጠቃላይ ሆስፒታል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ “ደህንነቱን የጠበቀ የጤና ክብካቤ ለሁሉም ጨቅላ ህፃናትና ህፃናት” በሚል መሪ ቃል፣ 7ኛውን ዓመታዊ “የዓለም የታካሚዎች ደህንነት ቀን”  በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ኹነቶች  አክብሯል።

የሆስፒታሉ መሥራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ከበደ ኦሊ በሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የህክምና ሳይንስ በትክክል ሲተገበር ከተዓምር የሚስተካከል ውጤት እንደሚያመጣ ገልጸው፤ “የምንሰጠው ህክምና የሚፈውስ እንጂ የሚጎዳ እንዳይሆን መትጋት ይገባል” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ለህሙማን ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር የተቋማትና የባለሙያ እንዲሁም የሌሎች አጋሮችን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አመልክተዋል።

ላንድማርክ አጠቃላይ ሆስፒታል  ለአስተማማኝ የህክምና ተግባራትና ቀጣይነት ያለው መሻሻል በማያወላውል ቁርጠኝነት አፅንዖት ሰጥቶ በመስራት ይገኛል ።

ከ3 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እያካሄደ የሚገኘውን የማስፋፊያ ፕሮጀክት የዓለም አቀፍ  የታካሚ ደህንነት መስፈርቶችን ባማከለ መልኩ በማከናወን  ለጤና አጠባበቅ ልህቀት ያለውን የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት እንደሚያረጋግጥ ገልፀዋል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶ/ር ፋህሚ አህመድ በበኩላቸው፤  የታካሚዎችን ደህንነት ለማሳለጥና የጤና አጠባበቅ አሰጣጥን ለመምራት የአለም አቀፍ የደህንነት ደረጃዎችና መመዘኛዎች ያላቸውን ጠቀሜታ አስምረውበታል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮን ወክለው የተገኙት አቶ መልካሙ ጥሩነህ፣ በከተማ አስተዳደሩ የታካሚዎች ደህንነት ማስጠበቅ እርምጃዎች አፈጻጸም ላይ ንግግር አድርገዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ደኤታ ሰሀረላ አቡዱላሂ በበኩላቸው፤ መንግስት ለታካሚዎች ደህንነት የሚሰጠውን ትኩረት እንደ አገራዊ የጤና ክብካቤ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው፤ ከ10 ታካሚዎች አንዱ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ህክምና የሚጎዳ ሲሆን፤ አሁን ባለን አቅም ደህንነቱ ባልተጠበቀ ህክምና ከሚደርሱ ጉዳቶች 50 በመቶውን መከላከል ይቻላል ተብሏል፡፡

በጨቅላ ህጻናት ላይ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ህክምና ከሚደርሱ ጉዳቶች መካከል ደግሞ ከ50 በመቶ እስከ 97 በመቶውን መከላከል እንደሚቻል ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ተጠቁሟል፡፡ ይህም ሁኔታውን ተስፋ ሰጪ ያደርገዋል ነው የተባለው፡፡

በላንድማርክ አጠቃላይ ሆስፒታል በተከበረው 7ኛው የዓለም የታካሚዎች ደህንነት ቀን  ላይ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት  ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ቀንአ ያደታ፣ የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርአያ ፣ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ  ሰሀረላ አቡዱላሂ ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶ/ር ፋህሚ አህመድ ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ተወካይ አቶ መልካሙ ጥሩነህና የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማት (ተወካዮች )፣ የኤምባሲ ከፍተኛ ሀላፊዎች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም  ተገኝተዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...

የአህጉሪቱን የርስ በርስ ንግድ ልውውጥ 250 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቀደ

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ፀሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ...

በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም

አሜሪካ እና ኢራን በተስማሙበት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ...