ሰበር ሰሚ ችሎት የጋዜጠኛ ተስፋለም የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ወሰነ

Date:

የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጉዳዩን ከተመለከተው በኋላ “የሥር ፍርድ ቤቶች የጋዜጠኛውን የዋስትና መብት መጠበቃቸው መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ያልተፈፀመበት እና ሕግን የተከተለ ሆኖ ስላገኘነው የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ አጽንተናል” የሚል ውሳኔ መስጠቱን የጋዜጠኛዉ ጠበቃ ቤተማርያም ዓለማየሁ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።


ይህ ማለት ጉዳዩ ሰበር ሰሚ ችሎት “አያስቀርብም” የሚል ትርጉም ያለው መሆኑን የገለፁት ጠበቃው፤ ችሎቱ ላይ ቢቀርቡም ፖሊስ ስለ ይግባኙ ከተጠየቀ በኋላ እሳቸው “መልስ እንዲሰጡበት አልተደረገም” ብለዋል።ዳኞች መዝገቡን ከተመለከቱና የሚጣራውን ካጣሩ በኋላ ጋዜጠኛው “ከዚህ በላይ መቆየት [በእሥር] የለበትም” ማለታቸውንም ጠበቃው አክለው ገልፀዋል።

ጠበቃ ቤተማርያም ዓለማየሁ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ “እንደሚፈታ እንጠብቃለን” ሲሉም አክለው ገልፀዋል።ዛሬ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር (EMMPA) ፖሊስ ይግባኝ የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም የጋዜጠኛውን የዋስትና መብት መንፈጉን “የጋዜጠኝነት ሙያን ጫና ውስጥ የመክተት ተግባር” አድርጎ እንደሚመለከተው አስታውቋል።

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ አንድ ጋዜጠኛ በሙያዊ ሥራው “የሰራው ጥፋት እንኳን ቢኖር ለተጨማሪ ምርመራ በእሥር ላይ እንዲቆይ ሳይገደድ፣ ከእሥር ውጪ ሁኖ ጉዳዩን መከታተል ይችላል” ሲል ያስታወሰው ማሕበሩ፤ ፖሊስ በጋዜጠኛ ተስፋዓለም ላይ የፈጸመው ተግባር “ይህንን አዋጅ የሚጥስ እና ጋዜጠኛው በሕግ የተሰጠውን የእሥር ከለላና የዋስትና መብት የሚነፍግ መሆኑ በእጅጉ አሳሳቢ ነው” ብሏል።

ድርጊቱንም “በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተቃጣ አደገኛ አፈና” አድርጎ እንደሚወስደው በመግለጽ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብቱ ተከብሮለት “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእሥር እንዲለቀቅ” ጠይቋል። የሙያ ማሕበሩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ጨምሮ የሚመለከታቸው ያላቸው ባለድርሻ አካላት ፖሊስ ለሕግ ተገዥ እንዲሆን ጫና እንዲፈጥሩ አሳስቧል።

በጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብት ላይ ፖሊስ ይግባኝ በማለቱ ትናንት ረፋድ ጉዳዩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ችሎት የታየ ሲሆን፣ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጽናት የጋዜጠኛው የዋስትና መብት እንዲከበር የወሰነ ቢሆንም መርማሪ ፖሊስ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማለቱ ጋዜጠኛው ከእሥር አልተፈታም።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተባለው የበይነ መረብ የመገናኛ ዐውታር መሥራችና ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ “ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት” በሚል ተጠርጥሮ እሑድ ሰኔ 1 ቀን 2017 በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋሉን ኢትዮጵያ ኢንሳይደርን የሚያስተዳድረው ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትናንት አስታውቋል።

DW Amharic

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...

ትራምፕ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር...