ሲፒጄ በአምስቱ ጋዜጠኞች ላይ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን ገለጸ

Date:

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሲፒጄ ለሶስት ዓመታት በእስር ላይ የሚገኙት አምስት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ በሽብርተኝነት ተግባር ላይ መሳተፋቸውን እንዲያምኑ እና ይቅርታ እንዲጠይቁ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን ገለፀ፤ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋዜጠኞቹን እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።

በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች ማለትም ጎበዜ ሲሳይ፣ መስከረም አበራ፣ ገነት አስማማው፣ ዳዊት በጋሻው እና አባይ ዘውዱ በ2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በሰሩት ዘገባ የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸዋል።

እንደ ሲፒጄ መግለጫ፣ የጋዜጠኞቹ ጠበቃ ስለሞን ገዛኸኝ አምስቱም ጋዜጠኞች የይቅርታ ደብዳቤውን ለመፈረም ወይም ለመጻፍ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ጋዜጠኞቹን ከሌሎች እስረኞች በመለየት በመንግሥት የቀረበውን የይቅርታ ረቂቅ ሰነድ ተከትለው የራሳቸውን ደብዳቤ እንዲያዘጋጁ ለማስገደድ ማስፈራሪያ እነዳደረሱባቸው ጠበቃው ገልጸዋል።

የቀረቡት የይቅርታ ደብዳቤዎች ጋዜጠኞቹ መንግሥት «ጽንፈኛ» ሲል ከጠራው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ለደረሰው ውድመት፣ ለሰው ሕይወት ማለፍ እና ለችግሩ «ኃላፊነት እንዲወስዱ»፣ ወደፊት መሰል እንቅስቃሴዎች ላይ እንደማይሳተፉ ቃል እንዲገቡ እና ስምምነቱን ካፈረሱ የሚወሰደውን እርምጃ እንዲቀበሉ የሚያስገድዱ እንደሆኑ ጠበቃው አብራርተዋል።

የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋዜጠኞቹ ፍርድ ቤት ውድቅ ያደረጉትን ወንጀል እንዲያምኑ ለማድረግ እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።

«ባለሥልጣናት አምስቱን ጋዜጠኞች ማዋረድ እና ማላገጥ ማቆም አለባቸው» ያሉት ሙቶኪ፣ ክሱ እንዲነሳና ጋዜጠኞቹ ተፈተው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ሲፒጄ በተጨማሪም ከአማራ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ሌሎች ከ300 በላይ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና አካላት መሰል የይቅርታ ደብዳቤ እንዲፈርሙ መጠየቃቸውን የሚገልጹ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ጠቅሷል።

ከእነዚህም ውስጥ 30 የሚሆኑ እስረኞች በሕግ ፊት እራሳቸውን ወንጀለኛ አድርገው እንደማያቀርቡ በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸው ተነግሯል።

በጋዜጠኞቹ ላይ የተመሰረተው የሕግ ሂደት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው የካቲት ወር በጎበዜ፣ መስከረም፣ ገነት እና ዳዊት ላይ የቀረበው የጋራ ክስ ሰፊ ማስረጃ ስላለው ሂደቱ እንዲቀጥል ብይን ሰጥቶ ነበር።

የተከሳሾች የመከላከያ ምስክር መስሚያ ቀጠሮ በተደጋጋሚ የተራዘመ ሲሆን፣ አሁን ግን ለኅዳር 10 ቀን 2019 ዓ.ም. ተቀጥሯል ።

በአባይ ዘውዱ ላይ የተመሰረተው ክስ ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ያስከስሳል ወይስ አያስከስስም በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም. ተቀጥሯል። ጋዜጠኞቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የእድሜ ልክ እስራት ወይም የሞት ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል።

ጠበቃው የመንግሥትን የይቅርታ ሂደት ተቃውመዋል ያለው ሲፒጄ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ይቅርታ የሚደረገው ፍርድ ከተሰጠ እና የመጨረሻ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ፣ መዝገቡ ስላላተዘጋ ጋዜጠኞቹን በነጻ ለመልቀቅ ክሱ መቋረጥ ወይም ምህረት መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ድርጅቱ የፍትሕ ሚኒስቴርን እና የፌደራል ኮሙኒኬሽን አገልግሎትን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ እና ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የተላከው ኢሜይል ደግሞ ሳይደርስ መቅረቱን ገልጿል።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ አዲስ መግለጫ የወጣው ድርጅቱ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ሕጋዊ አሰራር እና ፍትሐዊ ፍርድ እንዲያገኙ በተደጋጋሚ ጥሪ ማቀረቡን ተከትሎ ነው።

በየካቲት ወር ሲፒጄ በአማራ ክልል ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በሰሩት ዘገባ እና በሰጡት አስታየት ለሶስት ዓመታት ያህል በእስር ላይ ለሚገኙት ጎበዜ ሲሳይ፣ መስከረም አበራ፣ ገነት አስማማው እና ዳዊት በጋሻው ፍትሐዊ እና ግልጽ የሕግ ሂደት እንዲኖር ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ድርጅቱ ክሱ የእድሜ ልክ እስራት ወይም የሞት ቅጣት ሊያስከትል እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

ድርጀቱ እንዳስታወቀው፣ የ«አማራ ድምፅ» ጋዜጠኛ የሆነው ጎበዜ ሲሳይ በግንቦት 2015 ዓ.ም. በጅቡቲ ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ የተላከ ሲሆን፣ የኢትዮ ንቃት ሚዲያ መስራች መስከረም አበራ፣ የየኛ ሚዲያ ዘጋቢ ገነት አስማማው እና የአራት ኪሎ ሚዲያ አዘጋጅ ዳዊት በጋሻው ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከተያዙ ጋዜጠኞች መካከል ይገኙበታል።አስ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አቶ ይህንዓለም አቅናው የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆኑ

በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ እና ከፍተኛ የባለአክስዮኖች ቁጥር ካላቸው...

ማዕቀቦች የኢራንን የኒውክሌር መርሃ-ግብር ቢያደናቅፉም መንግስቱን ሊጥሉ እንደማይችሉ ተገለጸ

ማዕቀቦች የኢራንን ወታደራዊ እና የኒውክሌር እንቅስቃሴዎች አስቸጋሪና ውድ እንዲሆኑ...

የአፍሪካ ሀገራት አዲስ የኢንቨስትመንት ፈንድ ይፋ አደረጉ

በአፍሪካ ሀገራት ላይ የተደቀነውን ከፍተኛ የብድር ጫና ለማቃለል እና...

ዶናልድ ትራምፕ “በቅርቡ” ሆርሙዝ የአሜሪካ ግዛት አካል እንደሚሆን ተናገሩ

ከኢራን ጋር ያለው ግጭት እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካው...