ሴት ምሁራን ወደ አመራርነት እየመጡ አይደለም

Date:


በኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የሚገኙ ሴት ምሁራን ከወንድ አጋሮቻቸው እኩል ጥሩ የአካዳሚክ ውጤት አስመዝግበው ቢገኙም የከፍተኛ የአመራር ቦታዎች ላይ እንደማይታዩ አንድ ጥናት አመለከተ።


የኢትዮጵያ የሴቶች መብት ተሟጋች ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው ባለሙያዎች ምክረ ሀሣብ አቅርበዋል።


መጋቢት 3 2018 ዓ.ም በፕላቲኒየም ሆቴል በተካሄደ በዚህ የፓናል ውይይት እንደተመለከተው ሴቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተሳትፎ ቢኖራቸውም በውሳኔ ሰጭነት ቦታ ላይ ቁጥራቸው አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል።


በዕለቱ የጥናት ወረቀቱን ያቀረቡት ዶክተር ገነት ዘውዴ የቀድሞ ትምህርት ሚኒስትር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ፍሬህይወት ስንታየሁ ደግሞ ልምድና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።


እንደ አቅራቢዎቹ መረጃ በተለየ መልኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው በአመራር ደረጃ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ነው።በአንድ በኩል ሴቶች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገቡ ቢደረግም ባህላዊ እይታ ነግሶ በመቆየቱና ወንዶች ብቻ በመሪነት ስለሚታዩ አቅሙ እና የአመራር ክህሎትን ያዳበሩ ሴቶች ወደ ዩኒቨርስቲው አመራር ሲመጡ አይታይም ሲል ጥናቱ ድምዳሜ ያቀርባል።


ዶክተር ገነት ዘውዴ አኃዞችን በማቅረብ ሴት የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች በቁጥር 3 መሆናቸውን ጠቅሰው በአገራችን የሚነገሩ ተረትና ምሣሌዎችም የሴትን አለመቻል የሚያንፀባርቁ ስለሆነ ተፅዕኖው ቀላል እንደማይሆን አመልክተዋል።በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ75 አመት ታሪክ ውስጥ ሴት ፕሬዚዳንት ኖራ እንደማታውቅ ጥናት አቅራቢዋ አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ አመልክተዋል።


ሴት ምሁራን ወደ አመራር ቦታ ቀረብ እንዳይሉ የሚያደርጉ እንቅፋቶች በሦስት ደረጃዎች እንደሚታዩ ጥናቱ ያመለከተ ሲሆን ይህም በማህበራዊ ፣ መዋቅራዊና በግለሰብ ደረጃ ያሉ መሆናቸውን ጠቁሟል።


ከሦስቱ ውስጥ ማህበራዊ እንቅፋቶች ጎልተው የወጡ ሲሆን በተለይ ሴቶች በአስተዳደግም በሚፈጠሩ ተፅዕኖዎች የመሪነት ዕድሎቻቸው እንዳይሰፉ ይደረጋል።አጠቃላይ በማህበረሰቡ ውስጥ ስለ ሴት የመሪነት ሚና ያለው ምልከታ ሴቶች በከፍተኛ የአካዳሚክ አመራር ቦታ ላይ መድረሳቸውን እንደሚገድብ ጥናቱ ላይ ተመልክቷል።


በፓናሉ ላይ የተሳተፉ የፓርላማ አባላት፣የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች እና ሴት ምሁራን ሴቶች አቅሙና የትምህርት ዝግጅቱ እስካላቸው ድረስ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንትነትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የአመራር ቦታዎች የማይዙበት ምክንያት የለም፣ ይህን ለማድረግ በመንግሥትም ግልፅ ፓሊሲ ተቀምጦ፣የመተግበሪያ እና የተጠያቂነት አሠራር ተዘርግቶ ለተግባራዊነቱ መሠራት አለበት ሲሉ ሀሣብ ሰንዝረዋል።


የፓናሉ ውይይቱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ የሴቶች መብት ተሟጋች ዋና ዳይሬክተር ፌቨን አርአያ እንዳሉት የፓናል ውይይቱ አላማ ሴት ምሁራን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በአመራር ቦታዎች እንዲመጡ ማድረግ ነው።


ሴቶች ወደ አመራር ቦታ እንዳይመጡ ያደረጓቸውንም ተግዳሮቶች ለይቶ በማውጣት የመፍትሔ ሀሣብ መፈለግና ለተግባራዊነቱ ዕውን መሆን ሁላችንም የበኩላችን ማድረግ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የፓናል ውይይት እንዲሳካ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት መሆኑም ለማወቅ ተችሏል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት አካባቢ በቋሚነት መኖር የሚያስችላቸው 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ከበኦሞ...

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...