“በትግራይ በኩል ምንም ዓይነት የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ዝግጅት የለም” ሲል በቅርቡ ህጋዊ ሰውነቱ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) ገለጸ።
“የትግራይ ህዝብም ሆነ የአመራሩ ፍላጎት እና ተስፋ የቆዩም ሆኑ አዳዲስ ችግሮችና ልዩነቶች ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀራረብ በውይይት መፈታት የሚችሉ ናቸው የሚል ነው” ብሏል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የሀይማኖት አባቶች፣ ኤምባሲዎች፣ ሙሁራንና ባለሀብቶች “ትግራይ ወደ ግጭት፣ ጦርነት እንዳይገባ ስራችሁን አሁን ጀምሩ፤ ከተጀመረ በኋላ ብትናገሩ ዋጋ የለውም” ሲሉ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ማሳሰባቸው ይተዋሳል።
ህወሓት የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ማሳሰቢያ አስመልክቶ ዛሬ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የትግራይ ህዝብ ካሳና መልሶ ግንባታ እንጂ በደልና የጦርነት ማስፈራሪያ የሚገባው አይደለም” ብሏል።
የትግራይ ህዝብ፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር፣ ህወሓትና የትግራይ የጸጥታ አካላት ከሰላማዊ መንገድ ውጭ የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ምንም ዓይነት ዝግጅት እንደሌላቸው ለማረጋገጥ የሀይማኖት አባቶች፣ ሙሁራንና ባለሀብቶች መሬት ላይ በመውረድ እውነታውን ማየትና መታዘብ ይችላሉ” ሲል አስታውቋል።
ጥያቄያችን የፕሪቶሪያው ስምምነት ይተግበር፣ ተፈናቃዮችን ስደተኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቀያቸው ይመለሱ፣ የትግራይ ልዓላዊነት በህገ-መንግስቱ መሰረት ሙሉ በሙሉ ይረጋገጥ” የሚል ነው ብሏል፡፡
“ይህንን ማለታችን ለዘላቂ ሰላም ያለን ቁርጠኝነት እንጂ ጦርነት ናፋቂነትን በፍፁም ሊያሳይ ኣይችልም” ሲል ገልጿል፡፡
ህወሓት በመግለጫው “የፌደራል መንግስት ለሰላም ሂደቱ ዕንቅፋት በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ተጠምዷል” ሲል በመተቸት ወቀሳውን አቅርቧል።
ካነሳቸው ወቀሳዎች መካከልም “የፌደራል መንግስት ፖለቲካዊ ውይይት በመጀመር የቆዩ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ በአፋርና በምዕራብ ትግራይ በኩል ታጣቂዎችን በማሰልጠንና በመደገፍ” ላይ ይገኛል የሚለው ይገኝበታል።
“ወደ ትግራይ የሚገባ ነዳጅ በከፍተኛ መጠን ገደብ በማድረግ የክልሉ ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ክፉኛ እየጎዳው ነው” ያለው የህወሓት መግለጫ “እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በብሔራዊ ማንነታቸው ተለይተው እንዲታሰሩና እንዲሳደዱ እያደረገ ነው” ብሏል።
የትግራይ ህዝብ “በአገሪቱ ገደብ የለሽ መድልዎና መገለል እየተፈጸመበት እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል” ሲል አሳስቧል።
“በፕሪቶሪያው ስምምነት የተጀመረ የሰላም ሂደት ማጠናከር ፋይዳው በትግራይ ወይም ኢትዮጵያ ብቻ የተገደበ አይደለም ያለው የህወሓት መግለጫ “ለአከባቢው ህዝቦች በአጠቃላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው” ሲል አስታውቋል።
“የሰላም ሂደቱን የሚቃረን ሁኔታ ሲያጋጥም ደግሞ የአከባቢው ሰላምና ፀጥታ ወደ ችግር የሚያስገባ በመሆኑ የዓለም ማሕበረ-ሰብ የሰላም ሂደቱን ውጤታማ እንዲሆን ሀላፊነቱን እንዲወጣ” ሲልም አሳስቧል።
ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ለምክር ቤት አባሉ ጥያቄ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በትግራይ ጉዳይ በሰጡት ምላሽ “በዚህ በተከበረው ምክር ቤት አንድ መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው የሁሉም እምነት አባቶች፣ ሌላ ምንም ስራ የላችሁም በፍጥነት ትግራይ ወደ ግጭት እንዳይገባ፣ ወደ ጦርነት እንዳይገባ ስራችሁን አሁን ጀምሩ፤ ከተጀመረ በኋላ ብትናገሩ ዋጋ የለውም” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ከሐይማኖት አባቶቹ በተጨማሪም “ባለሃብቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ ሙሁራን፣ ኤምባሲዎች አሁን ውጊያ እንዳይጀመር” ሚናችሁን ተወጡ ሲሉ አሳስበዋል፤ “ምክንያቱም ከተጀመረ ከዚህ በፊት የምናውቀው አይደለም ይበላሻል ነገር” ሲሉ ገልጸዋል።
“በኛ በኩል በትግራይ ምድር አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለንም” ሲሉ የተደመጡት ጠ/ሚኒስትሩ “ከቻልን ማልማት ነው የምንፈልገው” ብለዋል። አስ
