በኬንያ ለቀናት የዘለቀው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ የ42 ሰዎች ህይወት ማለፉን መንግስት አስታውቋል።
ካለፈው ዓርብ ጀምሮ የጣለው ዝናብ በተለይ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የ26 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ በመላ ሀገሪቱም በመሰረተ ልማት እና በዜጎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።
የሀገሪቱ የልዩ ፕሮግራሞች ሚኒስትር ጄፍሪ ሩኩ እንደገለጹት፣ ጎርፉ መንገዶችን በማጥለቅለቅ የትራንስፖርት እና የእለት ተእለት እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ አስተጓጉሏል።
በናይሮቢ መደበኛ ባልሆኑ ሰፈሮች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እና ተሽከርካሪዎች በጎርፍ የተወሰዱ ሲሆን፣ የአየር በረራዎችም ወደ ሞምባሳ እንዲቀየሩ ተገደዋል።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተው፣ ወታደራዊ ሃይልን ጨምሮ የተቀናጀ የነፍስ አድን ስራ እንዲከናወን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
አሁንም ዝናቡ ሊቀጥል ስለሚችል ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የደህንነት አካላት እያሳሰቡ ይገኛሉ።
