በጋምቤላ ክልል በበጀት አመቱ በተከናወነው የገቢ አሰባሰብ ዙሪያ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
በቢሮዉ የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ሳሙኤል ገለታ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት በበጀት አመቱ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር።
በዚህም 5 .3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል በማለት አቶ ሳሙኤል ገልፀው በተገኘው ውጤት የእቅዱን 64 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንደተቻለ አስረድተዋል።
እስካሁን ድረስ በተሰበሰበው ገቢ ከ2017 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ2 ቢሊዮን በላይ ጭማሪ አሳይቷል።በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥሩ አፈፃፀም ተመዝግቧል ያሉት አቶ ሳሙኤል ይህን እውን ለማድረግ ለደንበኞች በሚሰጠው የአገልግሎት ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዪ ስራዎች ተከናውነዋል ሲሉ አክለዋል።
በተለይም የህገወጥ ምርቶች እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ተጨማሪ ጥረት ተደርጓል በማለት የተናገሩት ቡድን መሪው በጉምሩክ ሥርዓት ማሻሻያ መሰረት በርካታ ስራዎችን ማከናወን ተችሏል ሲሉ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።
