የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ተውኔት ማሳየት ሊጀምር እንደሆነ ተሰምቷል።
ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ባልተለመደ መልኩ ከተውኔት ደራሲያን እና ከተውኔት አዘጋጆች ጋር ልዩ ልዩ ስምምነቶችን ሲፈፅም የኤቨንት አዲስ ሚዲያ አዘጋጆች ተመልክተናል።
በዚህ የስምምነት ሥነሥርዓት ላይ ከተሰሙ ጉዳዮች በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያለው የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ከዓመታት በኃላ ተውኔት ማሳየት ሊጀምር እንደሆነ የተገለጸበት ጉዳይ አንደኛው ነው።
የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ወደ ወደ መደበኛው ስራ ሲመለስም የ”ባልቻ አባነፍሶ” ቴአትርን ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ አምርቶ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለተመልካች እንደሚያቀርብ ኤቨንት አዲስ ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
“ባልቻ አባነብሶ” ታሪካዊ ተውኔት እንዲዘጋጅም ስምምነት ተፈጽሟል። የዚህ አዲስ ድርሰት መራሔ ተውኔት በመሆን አዘጋጅ ዶ/ር ተሻለ አሠፋ የስምምነት ፊርማውን አስፍሯል።
ሌላ በኩል የደራሲ መልካሙ ዘሪሁን ድርሰት የሆነው “ወህኒ አምባ” የተባለውን አዲስ ወጥ ተውኔትን ወደ መድረክ ለማምጣት ስምምነት ተፈጽሟል።
ለዚህ አዲስ ድርሰት መራሔ ተውኔት በመሆን አዘጋጅ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ የስምምነት ፊርማውን አስፍሯል። የዚህ ተውኔትም ልምምድ በይፋ ተጀምሯል።’ወህኒ አምባ’ ተውኔት በሦስት ወራት ውስጥ ተሠርቶ እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት በ2018 ዓ.ም ለተመልካች የሚያቀርበውን የኦሮምኛ “ሰዴተ” የተሰኘ የሙሉ ጊዜ የኦሮምኛ ተውኔት ለመመድረክ ተስማምቷል።
