የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሕግ አገልግሎት መምሪያ በአቶ ትዝታው ሳሙኤል ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቋል።
የቤተ-ክርስቲያኒቷ ሕግ አገልግሎት መምሪያ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባቀረበው ክስ፤ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ የምርመራ መዝገቡ መብቱ ለሚፈቅድለት የዐ/ሕግ ዘርፍ እንዲተላለፍለፍ ጠይቋል።
በወንጀል ተጠርጣሪ /ተከሳሽ – አቶ ትዝታው ሳሙኤል ተጠርጣሪ /ተከሳሹ ነዋሪነቱን በውጪ ሃገር በማድረግ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ ውሳኔ ሰጪ አካልን ለማዋረድ፣ ለመስደብ እና የምዕመኑን ስሜት ለመንካት ብሎም በሀገሪቱ ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማሰብ በተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ መንገዶች እና ከ5 ሺሕ በላይ ተከታዮች ባሉት የራሱ የዪቲዩብ ቻናል በመጠቀም ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።
በማያያዝም ግለሰቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን አባቶችን፣ በየገዳማቱ ውስጥ የሚገኙ ገዳማውያን መነኮሳትና አገልጋዮችን “ግብረ ሰዶማውያን ናቸው” በማለት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን “የመተት እና ጠንቋይ ቤት ናት” በማለት ሲቀሰቅስ የቆየ መሆኑን መምሪያው ገልጿል፡፡
ግለሰቡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምትገለገልባቸውን ሃይማኖታዊ የፀሎት፣ የታሪክ፣ የገድላትና ድርሳናት መጻሕፍትን “ድውያን መጽሐፍት ናቸው መጥፋት አለባቸው” ማለቱን አስታውቋል።
“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቅድስና የምታከብራቸውንና የምትዘክራቸውን ቅዱሳን አባቶች እና እናቶችን ‘ጣኦታትና ጣኦት አምላኪ’ ናቸው በማለት ግለሰቡ የፈጸመውን የወንጀል አድራጎት በመጥቀስም ክስ መመስረቱን ቤተክርስቲያኒቷ ሕግ አገልግሎት መምሪያ አስታውቋል።
መምሪያው በአጠቃላይ ሰባት ነጥቦችን ያካተቱ የወንጀል ዝርዘርሮችን በመግለጽም ጉዳዩ፤ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ግለሰቡ በሕግ ተጠያቂ እንዲደረግ ባቀረበው አቤቱታ ጠይቋል።
