በአሶሳ ከተማ ያደገው የ19 ዓመቱ ታምረኛ ወጣት ኃይሌ አዳነ፣ እጅግ አስቸጋሪ የሚባሉ 11 የአሜሪካ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎችን የነፃ ትምህርት ዕድል ውድድር በአስደናቂ ሁኔታ ማሸነፍ ችሏል።
ኃይሌ ገና ከጅምሩ በራሱ ተነሳሽነት በኢንተርኔት የዌብሳይት ማበልጸግ (Web Development) የተማረ ሲሆን፣ የክረምት ወቅቶችን በመጠቀም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት (በአሜሪካና ዚምባቡዌ) የተሰጡ የኮዲንግ እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ስልጠናዎችን በተግባር ቀስሟል።
ይህን ያገኘውን ዕውቀት በመጠቀምም፣ የአየር ንብረት ድርቅን በ95% ትክክለኛነት አስቀድሞ መተንበይ የሚችል የAI ሞዴል የፈጠረ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያገለገለ የሚገኘውን ethioexam.et የተሰኘ የፈተና ዝግጅት መተግበሪያ ማበልጸግ ችሏል።
ይህ ድንቅ ብቃቱ በጠቅላላው የ4.1 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የነፃ ትምህርት ዕድል ያስገኘለት ሲሆን፣ እንደ ፕሪንስተን እና ፔንስልቬንያ ያሉ ትልልቅ ተቋማት ቢፈልጉትም እርሱ ግን የመጨረሻ ምርጫውን በቴክኖሎጂ ዘርፍ የዓለማችን ቁጥር አንዱ በሆነው MIT ላይ አድርጓል።
በመጪው ሐምሌ ወር ወደ አሜሪካ በማቅናት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ከፍተኛ ትምህርቱን የሚጀምረው ኃይሌ አዳነ፣ በቁርጠኝነትና በትጋት ለሚሰሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች በማንኛውም የዓለም አቀፍ መድረክ ላይ መወዳደርና ማሸነፍ እንደሚቻል ትልቅ ማረጋገጫና የሀገር ኩራት ሆኗል።
