የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት ኢራን ላይ እያካሄዱ ያለውን ጦርነት እንዲያቆሙ ያሳሰቡ ሲሆን ወታደራዊ እርምጃ በዲፕሎማሲ እንዲተካ ጠይቀዋል።
ጉተሬዝ በብራሰልስ እየተካሄደ ባለው የአውሮፓ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጦርነት ለማቆም ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።
በአሜሪካ እና በእስራኤል የተጀመረው ይህ ጦርነት ከቁጥጥር ውጪ የመውጣት ስጋት እንዳለው እና በንፁሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ መከራ እያደረሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዋና ጸሐፊው አክለውም የጦርነቱ ተፅዕኖ ከጦር ሜዳው ባለፈ እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸው፣ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው መዘዝ እጅግ አስከፊ ነው ብለዋል።
በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ አሳዛኝ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል በማስጠንቀቅ፣ ከጦርነት ይልቅ ዲፕሎማሲ የሚያሸንፍበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም አክለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት በተለይም በአውሮፓ የኃይል (ኢነርጂ) ዋጋ፣ በኢነርጂ ዋስትና እና በቀጠናዊ መረጋጋት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ላይ ለመወያየት ነው በብራሰልስ የተሰባሰቡት።
አሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም በኢራን ላይ መጠነ ሰፊ ጦርነት መጀመራቸውን ተከትሎ የዓለም የባሕር ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፤ የነዳጅ ዋጋ እንዲንር አድርጓል እንዲሁም የዓለም ኢኮኖሚ እየተናጋ መሆኑን ሽኑዋ ዘግቧል።
