አዲስ ስታንዳርድ ሚዲያ ንብረቶቹ በፀጥታ አካላት እንደተወሰዱበት አስታወቀ

Date:

የ“አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር፤ ባለፈው ቅዳሜ “በጸጥታ አባላት” ተይዞ ከአንድ ቀን በኋላ መለቀቁን አሳታሚ ድርጅቱ አስታወቀ።

ይህ ድርጊት በተፈጸመ በማግስቱ “የጸጥታ እና የደህንነት አባላት” ወደ “አዲስ ስታንዳርድ” ቢሮ በመግባት፤ መገናኛ ብዙሃኑ ለስራ የሚገለገልባቸውን ንብረቶች ይዘው መሄዳቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።

የመገናኛ ብዙሃኑ አሳታሚ ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ይህን የገለጸው፤ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 30፤ 2018 ባወጣው መግለጫ ነው።

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ የደረሱ ክስተቶችን በዝርዝር የያዘው መግለጫው፤ ከዋና አዘጋጁ እስር እና ከንብረቶች መወሰድ በተጨማሪ ድርጅቱ ላለፉት 16 ዓመታት በቢሮነት ሲጠቀምበት ከቆየው ህንጻ በሶስት ቀናት ውስጥ “በግዴታ እንዲለቅቅ” ቀነ ገደብ እንደተሰጠው አመልክቷል።

ድርጅቱን “ኢላማ ካደረጉ” ተከታታይ እርምጃዎች መካከል በቀዳሚነት የተፈጸመው የዋና አዘጋጁ ዮናስ እስር ነው።

ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 25 “በጸጥታ አባላት” የተያዘው ዮናስ፣ ከ24 ሰዓት ገደማ ቆይታ በኋላ መለቀቁን አሳታሚ ድርጅቱ ገልጿል።

ዋና አዘጋጁ ታስሮ በቆየበት ጊዜ “አካላዊ ጥቃት” እና “የተራዘመ ምርመራ” እንደተደረገበትም የድርጅቱ መግለጫ አክሏል።

በዋና አዘጋጁ ላይ ተፈጸመ የተባለው “እገታ”፤ በ“አዲስ ስታንዳርድ” ላይ ሲተገበር የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም።

የመገናኛ ብዙሃኑ ማኔጂንግ ኤዲተር የሆነው ሚሊዮን በየነ ባለፈው ሚያዝያ ወር “ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች” ከቢሮው ከተወሰደ በኋላ የደረሰበት ሳይታወቅ ለ20 ቀናት ታስሮ ቆይቷል።

Ethiopia insider

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ቴህራን ወሽመጡ ወዲያውኑ እንደማይከፈት አስጠነቀቀች

ኦማን ከኢራን ጋር በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ የምታደርገው ንግግር በጥሩ...

ከታክስ በፊት ከ1.54 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉን ስኬት ባንክ አስታወቀ

​ስኬት ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4.1 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ...