የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን “ጦርነቱ እንዲቆም እንድንወያይ አጥብቃ እየለመነች ነው፤ ካልሆነ ግን ይወድማሉ” ሲሉ ዛቱ።
ከሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ጋር ሆነው በዋይት ሐውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ናቸው” ያሉት ኢራናውያን “ከእኛ ጋር መወያየት ይፈልጋሉ” ብለዋል።
“ሆኖም ግን ትርጉም ያለው ውይይት የማይፈልጉ ከሆነ እኛ [መገናኘቱን] አንፈልግም” ሲሉም አክለዋል።
የየመን ሁቲ አማጺያን በሳዑዲ አረቢያ የባሕር እንቅስቃሴ ላይ የጣሉትን ክልከላ በተመለከተ “ሁቲዎች የሳዑዲን ወደብ ከዘጉ አሜሪካ ጉዳዩን ትፈታዋለች” ብለዋል።
ሁቲዎች ሳዑዲ አረቢያ ላይ የባሕር እንቅስቃሴ እገዳ መጣላቸውን አሳውቀዋል።
ከሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ጭነው በቀይ ባሕር በኩል ሲቀዝፉ የነበሩ ሁለት ግዙፍ መርከቦች ከየመን ታጣቂ ቡድን ሁቲ በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ምክንያት አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ መደረጋቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የሊባኖስ ፕሬዝዳንት በዋይት ሐውስ ትራምፕን አሞካሽተው “ጉብኝቱን ለረዥም ጊዜ ሲጠብቁት እንደቆዩ” ተናግረዋል።
የእስራኤል እና ሊባኖስ ጦርነት እስከ ወዲያኛው ያከትማል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው ይህም የትራምፕ “ሌጋሲ” ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ትራምፕ ለሊባኖስ ብዙ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እና አገሪቱ በሚገባት መጠን እንደሚያግዙ ተናግረዋል
