ኢራን ወደ ውይይት ካልተመለሰች የኃይል ማመንጫዎቿ እና ድልድዮቿ ላይ በቀጣይ ሳምንት ጥቃት እንደሚሰነዘር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠነቀቁ።
ትራምፕ ይህንን ያሉት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲሆን፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ ያቀረቡትን ሐሳብም ሰርዘዋል።
ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ የጣሉት እገዳ ግን ባለበት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
“በቀጣይ ሳምንት ነገሮች የከፉ ይሆኑባቸዋል። ወደ ድርድር ጠረጴዛው የማይመለሱ ከሆነ የኃይል ማመንጫዎቻቸውን እናፈርሳለን፤ ድልድዮቻቸውን እናፈርሳለን” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ባለሥልጣን ቮልከር ቱርክ የትራምፕን ዛቻ ኮንነዋል።
ትራምፕ በኢራን የሲቪሎች መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ለማድረስ መዛታቸው “በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ” መሆኑን ገልጸዋል።
“ሆነ ብሎ ንጹኃን ዜጎች ላይ እና መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት መፈጸም የጦር ወንጀል ነው” በማለትም አክለዋል።
