በቅርቡ የወጣው ‘የዕርዳታ ሰራተኞች ደኅንነት ሪፖርት 2025’፣ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ዕርዳታ ሰራተኞች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ከጨመረባቸው 10 የዓለም አገሮች አንዷ መሆኗን አመለከተ።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ በ2024 በኢትዮጵያ በደረሱ ጥቃቶች የ35 ሰዎች ሕይወት አልፏል። ምንም እንኳ በጋዛ እና በሱዳን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሞትና ጉዳት ቢመዘገብም፣ ኢትዮጵያም ለዕርዳታ ሰራተኞች ደህንነት አሳሳቢ ስፍራ ሆና ብቅ ብላለች።
በሀገሪቱ ውስጥ አብዛኛው ጥቃት የደረሰው በአማራ ክልል ሲሆን፣ ታጣቂ ቡድኖች የዕርዳታ ተሽከርካሪዎችንና ጭነቶችን ኢላማ በማድረግ እየጠለፉ ነው። ይህ ደግሞ የሚታፈኑ ሰዎችንና በትንሽ የጦር መሳሪያ ተኩስ የሚሞቱና የሚጎዱ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንዲል አድርጓል።
