ኢትዮጵያ “የሕይወት ክኅሎትን” በሥርዓተ ትምህርቷ ውስጥ ለምን አታካትትም?

Date:


ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም የሚያሳስበኝ ጥያቄ ነው። በተለይ የትምህርት ሥርዓትን ያጠናችሁ እና ጉዳዩ የሚመለከታችሁ የሙያ ባለሙያዎች ይህ ጽሑፍ ከደረሳችሁ፣ ሐሳብ ብትሰጡበት ደስ ይለኛል።

ለዚህ ጥያቄ ያነሳሳኝ በዙሪያችን የምንታዘበው፣ ነገር ግን ተገቢው ትኩረት ያልተሰጠው አሳሳቢ ማኅበራዊ እውነታ ነው። ቆም ብለን ዙሪያችንን ብናጤን፣ የችግሩን አግጦና አፍጦ መውጣት በየቀኑ እንታዘባለን።

​በማኅበረሰባችን ውስጥ ብዙዎች ሐሳቦቻቸውን በሰላማዊ፣ ግልጽና ጤናማ በሆነ መንገድ መግለጽ ሲሳናቸው ይታያል። የእርስ በርስ ግንኙነቶች በዚህ ሳቢያ ይሻክራሉ፤ ቤተሰብ ይበጠብጣሉ፣ አልፎ ተርፎም የአገርን ሰላም ያውካሉ።

ዛሬ በዙሪያችን የምናስተውላቸው ማኅበራዊ ቀውሶች ልዩ ገጠመኞች ሳይሆኑ፣ መደበኛ የዕለት ተዕለት ክስተቶች እየሆኑ መጥተዋል።

ሁላችንም በልጆቻቸው ጉዳይና በመሠረታዊ ፍላጎቶች ዙሪያ ብቻ ካልሆነ በቀር መነጋገር የማይችሉ ባለትዳሮችን እናውቃለን። ከጭቅጭቅና በነገር ከመቋሰል በቀር በሰላም መነጋገር የማይችሉ እህት ወንድማማቾች፣ ተጣልተው የማይጣሉ፣ ታርቀው የማይታረቁ ጓደኛማቾችና ፍቅረኛማቾች፣ እንዲሁም የሥራ ከባቢን ጤናማነት የሚበክሉ ጤናማ ያልሆኑ የሥራ ባልደረቦች ግንኙነቶች በዙሪያችን ሞልተዋል።

ስህተት ሲፈጠር ወይም ጥፋት ሲጠፋ ግልፁን ተነጋግሮ መፍትሔ በጋራ ከመፈለግ ይልቅ ስልካቸውን የሚያጠፉ፣ ወይም ሲደወልላቸው የማያነሱ፤ እመጣለሁ ብለው የሚቀሩ፤ የማይችሉትን ለማድረግ የሚስማሙ፣ ወዘተ፣ ሁሉም የችግሩ extensions ናቸው።

​የዚህ ሁሉ ቀውስ መንስዔ ያለንበትን ሁኔታ አጢኖ በሰላም የመነጋገርና የመደማመጥ ባሕል ማጣታችን ነው። ችግሩ በቤተሰብ ጀምሮ በአገር ይቋጫል። የሁለት የኅብረተሰብ ክፍሎች ግጭቶች የሁለት ቤተሰቦች ግጭቶች ግዙፍ አምሳያ ይመስለኛል።

ወላጆች የኑሮ ጫናንና የራሳቸውን ስሜታዊ ቀውስ ልጆቻቸውን በመውቀስና በመጨቆን ሊወጡት ይሞክራሉ። አፍቃሪዎች መርዛማ ለሆነው አጋራቸው ተገዢ በመሆን የእነሱን ይሁንታ ለማግኘት ሌት ተቀን ይደክማሉ። በሥራ ቦታ ደግሞ አለቆች በሥራቸው ያሉትን ሠራተኞች በሥልጣን እየበደሉና እያዋረዱ፣ ራሳቸውን እንደ tough leader ይቆጥራሉ።

በቋንቋችን ውስጥ ለእንዲህ ዓይነቱ “መርዛማ ግንኙነት” የሚሆን ትክክለኛ ሥያሜና ግንዛቤ እንኳን የለንም። እንዲያውም አንዳንዴ አንደኛው ሌላኛውን እስኪገድል ድረስ የሚፈጸመው ስሜታዊ በደል “እንደ ፍቅር መግለጫ” ሲቆጠር ይታያል።

በብዙ ግንኙነቶች በደል አድራሹ ራሱን እንደ በጥባጭ አይመለከትም፤ ተበዳዩም “ነገ ይስተካከላል” በሚል የሐሰት ተስፋ በስነ-ልቦና ጫና ውስጥ ይማቅቃል። ይህንን መርዛማ ግንኙነት ራሱን በቅጡ የሚያውቁትና የሚረዱት ጥቂቶች በመሆናቸው፣ ሁላችንም በማኅበራዊ ውዥንብር ውስጥ እንዳክራለን።

​ትምህርት ጥሬ ሐቅን፣ ቀመሮችን እና ንድፈ ሐሳቦችን በአዕምሮ ውስጥ ማከማቻ ብቻ መሆን የለበትም። ግለሰቦች በማኅበረሰብ ውስጥ በጤናማና በአዎንታዊ መንገድ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሕይወት ክኅሎትን ሊያስጨብጣቸው ይገባል።

የሥርዓተ ትምህርታችን መሠረታዊ የሕይወት ክኅሎቶችን ሊያስተምረን ይገባል። ትምህርት “እንዴት ከሰው ጋር በውጤታማ መንገድ ተነጋግረን መግባባት እንችላለን? ግንኙነታችን ሲሻክርና መርዛማ ሲሆን እንዴት ቀድመን ማወቅ እንችላለን? ክፍተቶች ሲፈጠሩ ምን አድርገን ማስተካከል እንችላለን? በግንኙነቶች ውስጥ ቀውስ ሲፈጠር መንስዔውንና መፍትሔውን እንዴት መለየት እንችላለን? እንዴት ከመርዛማ ግንኙነቶች ራሳችንን ማውጣት እንችላለን?” የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች መመለስ መቻል አለበት።

​በዓለም ላይ የሕይወት ክኅሎትን በሥርዓተ ትምህርታቸው ውስጥ ያካተቱ አገራት ቁጥር 145 ገደማ እንደደረሰ መረጃዎች ያሳያሉ፤ በዚህ ርዕስ ዙሪያ በርካታ የሥርዓተ ትምህርት ፍልስፍናዎችም ዳብረዋል።

በእኛም አገር የሕይወት ክኅሎት (Life Skills) ሥልጠና እንደ አንድ ራሱን የቻለ የትምህርት ዓይነት ቢካተት እና ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ በየደረጃው እያደገ የሚሄድ ሥርዓት ቢዘረጋለት ትልቅ የትውልድ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብዬ አስባለሁ።

ይህ ሲሆን መነጋገርና መደማመጥ የሚያውቁ የቤተሰብ አባላት፣ ጤናማ ጓደኛማቾችና ፍቅረኛሞች፣ እንዲሁም ጤናማ የሥራ ቦታዎች ይኖሩናል።

በዚህ ክኅሎት እጦት ሳቢያ የሚፈርሱ ትዳሮች፣ ቤተሰቦችና ማኅበራዊ ትስስሮች ይተርፋሉ። የነገሩ በጎ ተጽዕኖ ከግለሰብ ሕይወት አልፎ ለአገር ሰላምም ሊበጅ ይችላል የሚል እምነት አለኝ።
በፍቃዱ ዘሀይሉ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመረጃ ነጻነት አዋጅን በሙሉ ድምፅ አጸደቀ

በምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ...

በቬንዝዌላ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የ32 ሰዎች ህይወት አልፏል

በቬንዙዌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን 7.2 እና 7.5...

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ “ሉሲ” ላገኟት ፕሮፌሰር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጠ

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፥...

የሳህለወርቅ ዘውዴ አዲሱ አለም አቀፍ ሹመት በተመድ ልዩ ተልእኮ ተሰጣቸው

የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በተመድ ዋና ፀሀፊ...